“የገዢዎች  እብሪት እና ግፍ ካልቆመ ከፍተኛ አደጋ ይደርሳል” ሲሉ የጎንደር ነዋሪዎች አስጠነቀቁ

ሐምሌ  ፳፮ ( ሀያ ስድስት ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ለተለያዩ የመንግስት መስሪያ ቤቶች የተጻፈውና በቅጅ ለኢሳት የተላከው ደብዳቤ ፣  “ በእብሪተኛ ገዢዎች እየተፈጸመ ያለው ግፍ በሃገርና በህዝብ ላይ የደገሰውን የሞት ድግስ ከማድረሱ በፊት የሚመለከታቸው ወገኖች ሁሉ አፋጣኝ መልስ እንዲሰጡ እንጠይቃለን ብሎአል።

ደብዳቤው በጎንደር ባለፈው እሁድ ተካሂዶ በነበረው የተቃውሞ ሰልፍ ላይ የቀረቡት ጥያቄዎች በአፋጣኝ መልስ እንዲያገኙ ይጠይቃል። በግፍ ታፍነው የተወሰዱት የወልቃይት የማንነት ጥያቄ አቅራቢ ህዝብ ወኪሎች የሆኑት አቶ አታላይ ዛፌ፣ አቶ ጌታቸው አደመ፣ አቶ አለነ ሻማ፣ አቶ መብራህቱ ጌታሁንና ሌሎችም የተጣለባቸውን የህዝብ አደራ አቤቱታ በሰላማዊና ህጋዊ መንገድ ለመንግስት ከማቅረባቸው ውች ሌላ ምንም ከህዝብ እይታ የተሰወረ የሰሩት ወንጀል ሳይኖር ሆን ተብሎ የጥያቄውን መስመር ለማስቀየር የሃሰት ውንጀላ በመሆኑ በአስቸኳይ እንዲለቀቁ ይጠይቃል።

የወልቃይት አማራ ማንነት ጥያቄ በአስቸኳይ እንዲፈታ፣ ከ2007 ዓም ጀምሮ በሰሜን ጎንደር በአንድነት የሚኖሩ ቤተሰቦችን አማራ ቅማንት የሚል ከፋፋይ ሴራ በመፍጠር በተለያዩ ጊዜ በሽፋን ጭልጋ ትክል ድንጋይ ሮቢት ማውራና ሌሎች ቦታዎች ለሞቱትና ያለ አገባብ ለታሰሩት ወንድሞችንና እህቶች የሃሳቡ ጠንሳሾች፣ አስፈጻሚና ፈጻሚ ተጠያቂዎች ለፍርድ እንዲቀርቡ፣ ሃምሌ 5 2008 ዓም በጎንደር ደህንነትና ጸረ ሽብር ግብረ ሃይል በመግለጫ ያስተላለፉት መልእክት ፍጹም የተሳሳተና ውሸት በመሆኑ ማስተባበያ በመስጠት የኢትዮጵያን ህዝብ ይቅርታ እንዲጠይቁም ደብዳቤው ይጠይቃል።

“ከዚህ በሁዋላ በኦሮምያ ጋምቤላ ቤንሻንጉልና ሌሎችም የኢትዮጵያ መሬቶች በኢትዮጵያውያን የሚቀርቡ ሰላማዊ ጥያቄዎችን በተጠየቁበት በሰላማዊ መልስ ከመስጠት ውጭ ሻዕቢያ ቅጠረኛ ሽብርተኛ የሚል የሃሰት ስም በመለጠፍ እራሱ በሚከፍላቸው ሰራዊቶች፣ በእራሱ ገንዘብ በተገዛ መሳሪያ በማፈን በመግደል ሰላማዊ ጥያቄዎችን ለመድፈቅ እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ እንዲቆምና እንዳይሞከር በጥብቅ እናሳስባላን” የሚለው ደብዳቤው ፣ ለእነዚህ ጥያቄዎች አፋጣኝ መልስ እንዲሰጠም ጠይቋል።

የሳንጃ ነዋሪዎች እና ታጣቂዎች ጎንደር ከተማ ገብተው የተቃውሞ ድምጻቸውን ካሰሙ በሁዋላ ወደ ቤታቸው ሲመለሱ ምሽት ላይ ህዝቡ በጀግና አቀባባል ተቀብሎአቸዋል።

በጎንደር እና በእስቴ ወረዳ በመካነየሱስ ከተማ  የተካሄዱትን ተቃውሞዎች ተከትሎ ተመሳሳይ ተቃውሞች በመጪው እሁድ በባህርዳር ፣ በደብረታቦር እንዲሁም በመካነሰላም  በድጋሜ ለማካሄድ ዝግጅቶች እየተካሄዱ ነው። ሰልፎቹ በጎንደር የሚካሄደውን ህዝባዊ ተቃውሞ ለመደገፍ የተጠራ ነው።