ሐምሌ ፳፮ ( ሀያ ስድስት ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በደቡብ ጎንደር ዞን በእብናት እና ፋርጣ ወረዳዎች ከ2 ቢሊዮን 400 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ገንዘብ የሚገነባው ርብ የመስኖ ግድብ ተደርምሶ በ60 ሰዎች እና በንብረት ላይ ጉዳት አድርሷል። ግድቡ በ2 ሺ ዓም የተጀመረ ሲሆን፣ በአራት አመት ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ ቢጠበቅም ከ8 አመታት በሁዋላም ግንባታው አላላቀም። ግድቡ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ሰራተኞች ማኔጂመንቱ የሚፈጽመውን ሙስና ሲያጋልጡ ቢቆዩም እርምጃ የሚወሰድ አካል አልነበረም።
ከፍተኛ ገንዘብ የወጣበት ግንባታ ከመዘግየቱ አልፎ መፍረስ መጀመሩ የአካባቢውን ህዝብ አስቆጥቷል።
ግንባታውን የሚያካሂደው የኢትዮጵያ ውሃ ስራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት ሲሆን በ1 ቢሊዮን 300 ሚሊዮን ብር ወጪ ለማጠናቀቅ እቅድ ነበረው ሆኖም በተለያዩ ምክንያቶች ወጪው በእጥፍ ጨምሯል። ያም ሆኖ ግንባታው ፈቅ ሳይል መደርመሱ በአገሪቱ ውስጥ የሚሰሩ የመስኖና ሌሎች ግንባታዎችን ጥራት ጥያቄ ውስጥ አስገብቶታል።