ኢሳት (ሃምሌ 25 ፥ 2008)
የወልቃይት ህዝብ የማንነት ጥያቄ በነሱ የኮሚቴ አባላት ላይ የተወሰደው እርምጃ በመቃወም እንዲሁም የወልቃይት ህዝብ የአማራነት ጥያቄው ምላሽ እንዲያገኝ በመጠየቅ ዕሁድ ሃምሌ 24 ፥ 2008 በጎንደር የተካሄደው ህዝባዊ ትዕይንት በደማቅ ሁኔታ ተጠናቀቀ።
መሰል ተቃውሞ ሰልፍ በደቡብ ጎንደር እስቴ የተካሄደ ሲሆን፣ ህዝቡ ህዝባዊ ጥያቄዎችን ሲያሰማ ማርፈዱ ተመልክቷል።
የወልቃይትን ህዝብ የማንነት ጥያቄ ከማስተጋባት ባሻገር በኢትዮጵያ በተለያየ መንገድ በደል ደሶባቸው ያሉትን የህብረተሰብ ክፍሎች በማንሳት አጋርነታቸውን የገለጹት የጎንደር ከተማና አካባቢዋ ነዋሪዎች በኦሮሚያ ክልል የቀጠለው ግድያ እንዲሁም የታሰሩ የሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላትና ሌሎች የህሊና እስረኞች እንዲፈቱ ጥሪ አቅርበዋል።
የመንግስት ሃላፊዎች ሰላማዊ ሰልፍ አልተፈቀደም በማለት በመገናኛ ብዙሃን ለመከልከል የሞከሩ ቢሆንም፣ የሰልፉ አስተባባሪዎች ማሳወቅ እንጂ ማስፈቀድ አይጠበቅብንም በማለት፣ ሰልፉ እንደማይቀር ባረጋገጡት መሰረት ደማቅ ትዕይንት ህዝብ ተካሄዷል።
በውጭ ሃገር የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ሂደቱን ከኢሳትና መሰል የኢትዮጵያውያን መገናኛ ብዙሃን እንዲሁም በማህበራዊ ሚዲያዎች ሲከታተሉ ቆይተዋል። አርማ የሌለበት የኢትዮጵያ ባንዲራ በ10 አመት ጊዜ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ ምድር ተውለበለበ በማለት አስተያየት የሰጡ ታይተዋል።
ትዕይንቱን ያስተባበሩት ወገኖች ጀግንነትና አርቆ አስተዋይነት አድናቆታቸውን የገልጹ ብዙዎች ሲሆኑ፣ የጎንደር ህዝብ ከወልቃይት ህዝብ ጥያቄ ባሻገር የሌሎች ኢትዮጵያውያንም ጥያቄ በማስተጋባት ለሰዓታት ያካሄደውን ትዕይት በደመቀ ሁኔታ ማጠናቀቁ ታወቋል።
በተመሳሳይ ዜና በደቡብ ጎንደር እስቴ ከተማ የሚኖሩ የአካባቢው ተወላጆች የወልቃይት ህዝብ የማንነት ጥያቄ ላነሱ የኮሚቴ አባላት በዕይንቱ ህዝብ ድጋፋቸውን ገልጸዋል። የታሰሩ የኮሚቴ አባላት እንዲፈቱም ጥያቄ አቅርበዋል።