ህዳር 7 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ስሎቫኪያ በኢትዮጵያ ታስረው የነበሩትን አምባሳደሯን አስመልክቶ በኢትዮጵያ መንግስት የተሰጣት ማብራሪያ በቂ ስላልሆነ ተጨማሪ ማብራሪያ እንዲሰጣት አጥብቃ ጠይቃለች።
“ ዘ ስሎቫክ ስፔክታተር” የተባለው የስሎቫኪያ ጋዜጣ እንደዘገበው፤ በኢትዮጵያ ፀጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ሥር ውለው ለሁለት ቀናት ከታሰሩ በኋላ የተለቀቁት በኢትዮጵያ የስሎቫኪያ አምባሳደር፣ በጉዳዩ ዙርያ ከስሎቫክ ባለሥልጣናት ጋር ለመመካከር ወደ አገራቸው ተመልሰዋል ፡፡
አምባሳደር ሚላን ዱብቼክ ከመኖሪያቸው ወጥተው የእግር ጉዞ እያደረጉ ሳለ ጥቅምት 25 ቀን 2004 ዓ.ም. በኢትዮጵያ የፀጥታ ኃይሎች መያዛቸውን የገለጸው ጋዜጣው፣ ከሁለት ቀናት እስር በሁዋላ ጥቅምት 27 ቀን 2004 ዓ.ም. በአውሮፓ ኅብረት ጣልቃ ገብነት መለቀቃቸውን አመልክቷል፡፡
እንደ ዘ ስሎቫክ ስፔክታተር ዘገባ፤ ኢትዮጵያ ስለጉዳዩ ማብራርያ እንድትሰጥ ጠይቆ የነበረው የስሎቫኪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ጀርመን በሚገኘው የስሎቫኪያ ኤምባሲ በኩል የደረሰው ማብራርያ በቂ እንዳልሆነ ገልጿል፡፡
የስሎቫኪያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሚኩላስ ዙሪንዳ የኢትዮጵያ መንግሥት የሰጠውን ማብራርያ የመረመሩት ቢሆንም፣ ምላሹ እንዳላረካቸው ለጋዜጣው ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ በሰጠችው ማብራርያ ውስጥ የሚገኙት አንዳንድ አባባሎች የይቅርታ ይዘት ያላቸው ቢሆኑም፤ ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ስሎቫኪያን በይፋ ይቅርታ እንዳልጠየቀች ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በቪየና ኮንቬንሽን መሠረት የዲፕሎማቲክ ከለላ ያለውን አምባሳደር በማሰር ለፈጸመችው ድርጊት በአጭር ጊዜ ውስጥ በአጥጋቢ ሁኔታ ማብራሪያ ልትሰጥና በይፋ ይቅርታ ልትጠይቅ እንደሚገባ ሚኒስትሩ አሣስበዋል።
እስካሁን አምባሰደሩ በምን ምክንያት እንደታሰሩ ለማወቅ አለመቻሉንም፤ ከጋዜጣው ዘገባ ለመረዳት ተችሏል፡፡