ኢሳት (ሃምሌ 21 ፥ 2008)
በኦሮሚያ ክልል በአርሲ ዞን በሮቤ ወረዳ ሰባት የአንድ ቤተሰብ አባላት በምግብ መመረዝ ምክንያት መሞታቸውን የክልሉ ፖሊስ ሃሙስ አስታወቀ።
የልጆች እናት የሆኑትና ስማቸው ያልተጠቀሰው እማወራ በከተማዋ ከሚገኝ አንድ ሱቅ የገዙት ነጭ ዱቄትና እርሾ ለቤተሰብ አባላቱ ሞት ምክንያት መሆኑን የክልሉ ባለስልጣናት ዋቢ በማድረግ የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
የልጆቹ እናት ዱቄቱን በእርሾው አዘጋጅተው (አቡክተው) ካደሩ በኋላ በተረፈው እርሾ የጋገሩትን እንጀራ ተመግበዋል የተባሉ ስድስት የቤተሰቡ አባላትና አንድ የጎረቤት ልጅ ሊሞቱ መቻላቸው ተገልጿል።
ይሁንና በዕለቱ የቤተሰቡ አባወራና የቀበሌ ሊ/መንበር የሆኑት አቶ ፉአድ ወደ መኖሪያ ቤታቸው አምሽተው በመግባታቸውና እራታቸውን ባለመብላታቸው ከአደጋው ሊተርፉ መቻላቸውን የወረዳዋ ፖሊስ አስታውቋል።
ከአደጋው የተረፉት አባወራ የቤተሰቡ አባላት ሲያጣጥሩ በመስማታቸው ወደ ሆስፒታል ለመውሰድ ቢሞክሩም የቤተሰብ አባላቱ ሊተርፉ አለመቻላቸው ታውቋል።
በተያያዘ ዜናም አርሲ ሮቤ ከተማ ከሚገኝ አንድ ሻይ ቤት ምግብ ተመግበዋል የተባሉ 46 ሰዎች በጠና ታመው ሆስፒታል መግባታቸውንና ከህክምና በኋላ ወደ ቤታቸው መሄዳቸውን ባለስልጣናት ገልጸዋል።
በምግብ መበከሉ ጉዳት ከደረሰባቸው መካከል አንደኛው ግለሰብ አሁንም ድረስ በህክምና ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ ከአንድ ሱቅ የተገዛ እርሾ ለአደጋው መጠርጠሩን የዞኑ የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት አመልክቷል።
በአካባቢው የደረሰን አደጋ ተከትሎ በህመም ምክንያት ሆስፒታል ቆይቶ ነበር የተባለ የሱቁ ባለቤት በቁጥጥር ስር ውሎ ምርመራ እየተካሄደበት መሆኑን ከሃገር ቤት ከተገኘ መረጃ ለመረዳት ተችሏል።