በሃመር ወረዳ የሚኖሩ አርብቶ እና አርሶ አደር ማህበረሰቦች ለመንግስት ግብር መክፈል ማቆማቸውን ገለጹ

ኢሳት (ሃምሌ 20 ፥ 2008)

በደቡብ ክልል ሃመር ወረዳ ስር የሚገኙ በርካታ አርብቶ እና አርሶ አደር ማህበረሰቦች በመንግስት አስተዳደር ላይ ተቃውሞን በማቅረብ ግብር መክፈል ማቆማቸውን የአካባቢው እማኞች ለኢሳት ገለጹ።

የማህበረሰቡ አባላት በተለያዩ ጊዜያት የሚያነሷቸው አስተዳደራዊ ጥያቄዎች በቂ ትኩረትና ምላሽ ባለማግኘታቸው ምክንያት ነዋሪዎቹ ግብርን ጨምሮ ከመንግስት በብድር የቀረበላቸውን የምርጥ ዘር ክፍያ ላለመክፈል መወሰናቸውን ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ ነዋሪዎች ከዜና ክፍላችን ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ አስረድተዋል።

በደቡብና ሰሚን አሪ አካባቢ የሚገኙ አርብቶና አርሶ አደር ነዋሪዎች በአካባቢያቸው ለ25 አመታት ያህል ምንም አይነት ለውጥ ባለማየታቸው ምክንያት የራሳቸውን እርምጃ እየወሰዱ መሆናቸውን ከነዋሪዎቹ ለመረዳት ተችሏል።

ህዝቡ ራሱን እያስተዳደረ ነው ሲሉ የተናገሩት እማኞች፣ በአካባቢው የሚገኙ የመንግስት አካላት ነዋሪው ያለበትን የግብር እዳ እንዲከፍል ማግባባት ለማድረግ ቢጥሩም ያለውጤት መበተኑን እማኞች ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ አስታውቀዋል።

ባለፈው አመት በጂንካ አካባቢ ተመሳሳይ አስተዳደራዊ ጥያቄ ተነስቶ ግጭት በማስከተሉ በርካታ ነዋሪዎች መገደላቸው የሚታወስ ሲሆን፣ በጂንካ ከተማ ዙሪያዋ ባሉ ወረዳዎች ውጥረቱ እልባት አለማግኘቱ ታውቋል።

አርብቶና አርሶ አደር ነዋሪዎቹ ግብር ችለመክፈል በመወሰናቸው የደረሰባቸው ተፅዕኖ እንዳለ የተጠየቁ እማኞች “ድሮም የምናገኘው ነገር የሌለ በመሆኑ ውሳኔያቸን ያመጣብን ተፅዕኖ የለም” ሲሉ ምላሽን ሰጥተዋል።

በስልጣን ላይ ያለው መንግስት ጉልበቱ በከተሞች ላይ ነው ሲሉ የገለጹት የአካባቢው ነዋሪዎች በመንግስት አስተዳደር ላይ ተቃውሞን እያቀረቡ ያሉ ነዋሪዎች ቁጣቸውን በተለያዩ መልኮች እየገለጹ መሆኑን አክለው ገልጸዋል።

የደቡብ ክልልን ጨምሮ በተለያዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች ነዋሪዎች በመንግስት ላይ የሚያቀርቡት ተቃውሞ እየተጠናከረ መምጣቱን ፍሪደም ሃውስ የተሰኘ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ሰሞኑን ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።