ሐምሌ ፳ ( ሀያ ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በሰሜን ጎንደር የተጀመረውን ህዝባዊ አመጽ ተከትሎ ከፍተኛ ድንጋጤ ውስጥ የገባው የ ህወሃት /ኢህአዴግ አመራርና ክልሉን የሚያስተዳድረው ብአዴን፣ እንቅስቃሴውን ለማብረድ ከትናንት በስቲያ ጎንደር ከተማ ውስጥ ከተወሰኑ የወልቃይት የአማራ ማንነት የኮሚቴ አባላት፣ ከታዋቂ ሰዎችና ከአገር ሽምጋሌዎች ጋር ያደረገው ስብሰባ ያለውጤት ተበትኗል።
ነባሩ የብአዴን ታጋይ እና የጠ/ሚኒስትሩ አማካሪ አቶ በረከት ስምዖን፣ የክልሉ ፕሬዚዳንት ገዱ አንዳርጋቸውና ምክትላቸው አቶ ብናልፍ አንዷለም ስብሰባውን መርተዋል። በስብሰባው ላይ የተሳተፉት ሰዎች ብአዴን በህወሃት እያስጠቃቸው መሆኑን የተለያዩ መረጃዎችን በማቅርብ ተናግረዋል።
ህወሃት ድፍረት በተሞላበት መንገድ በክልላችን ገብቶ ሰዎችን አፍኖ ለመውሰድ ያደረገውን ሙከራ በመቃወማችን ሽብረተኞች ተብለን በመንግስት የመገናኛ ብዙሃን ተብጠልጥለናል በማለት የተናገሩት ተሳታፊዎች፣ ይህም ዘገባ በይፋ እንዲስተባበልላቸው ጠይቀዋል። ዘገባውን ስህተት መሆኑን የገለጹት አቶ በረከት፣ ተሰብሳቢውን ይቅርታ ቢጠይቁም፣ ተሰብሳቢዎች ግን በአደባባይ እንደተዘለፍን በአደባባይ ይቅርታ እንጠየቅ የሚል አቋም አንጸባርቀዋል።
ሃምሌ 5፣ 2006 ዓም ታፍነው የተወሰዱ ወልቃይት ጠገዴ የአማራ ማንነት የኮሚቴ አባላት እንዲለቀቁ፣ በክልሉ የሚካሄደው ህገወጥ አፈና እንዲቆም፣ ከወልቃይት ጠገዴ ጋር በተያያዘ የታሰሩት ዜጎች እንዲፈቱ የሚሉና በርካታ ጥያቄዎች፣ ትችቶችና አስተያየቶች ቀርበዋል። መድረኩን የመሩት የአብዴን መሪዎች ለተነሱት ጥያቄዎችና አስተያየቶች በቂ መልስ ሳይሰጡና ተሰብሰባዊውን ሳያረኩ ስብሰባው ተጠናቋል።
በሌላ በኩል የቀድሞዋ የህወሃት ታጋይ የነበሩት ታጋይ ርስቴ መብራቱ በኢሳት የሰጡት ቃለምልልስ በአካባቢው ህዝብ ከፍተኛ ተቀባይነት ማገኘቱና መነቃቃት መፍጠሩ ታውቋል። ግለሰቡዋን በቅርበት የሚያውቋት ሰዎች እንደተናገሩት ታጋይ ርስቴ የወልቃይትን ህዝብ ከጨፈጨፈው ህወሃት ጎን ቆማ በመታገሏ የአካባቢው ህዝብ አዝኖባት የነበረ ቢሆንም፣ አሁን ግን በቃለምምልሷ ህዝቡን መካሱዋን እና ከፍተኛ የመነቃቃት ስሜት መፍጠሯን ተናግረዋል።
ታጋይ ርስቴ ”ከህወሀት ጎን ተሰልፌ የተዋጋሁት ለህዝቤ ባርነትን ለማምጣት አልነበረም። ማንነቴ ተቀይሮ ሌላ ለመሆን አልነበረም። ይጸጽተኛል። ለህዝቤ ባርነትን ካመጣ ስርዓት ጋር ተሰልፌ የልጅነት እድሜዬን መጨረሴ ይቆጨኛል። የኢትዮጵያን ህዝብ ይቅርታ እጠይቃለሁ” ማለቷ ይታወቃል።
የአካባቢው ህዝብ የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር ባለቤትና የኢፈርት ስራ አስኪያጅ አዜብ መስፍንም በተመሳሳይ መንገድ ወልቃይት ጠገዴ አማራ እንጅ ትግሬ አለመሆኑን እንድትናገርና የተሰራውን ደባ እንደ ታጋይ ርስቴ ታጋልጣላች ወደ ማንነቷም ትመለሳለች ብሎ እየጠበቀ ነው። ወ/ሮ አዜብ ቀድሞ ወልቃይት ጠገዴ ትግሬ ነው የሚል አቋም ሲያራምዱ ከቆዩ በሁዋላ፣ ካለፉት ሁለት አመታት ጀምሮ ግን ይዘውት በነበረው የተሳሳተ አቋም እያዘኑ እንደሚገኙና የኮሚቴው አባላትንም ሆነ ጥያቄውን የሚያቀረቡ ሰዎችን መተቸትና መንቀፍ ማቆማቸውን ከቤተሰቦቻቸው አካባቢ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
በእናታቸውም በአባታቸውም የወልቃይት ተወላጅ የሆኑት ወ/ሮ አዜብ በድፍረት ወጥተው አቋማቸውን ለህዝብ ግልጽ ባያደርጉም ከፍተኛ ብዥታ ውስጥ መግባታቸው ታውቋል።