ኢሳት (ሃምሌ 19 ፥ 2008)
ካይሮ በሚገኘው የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ኮሚሽን በራፍ ራሳቸውን ከአቃጠሉት ሁለት ኢትዮጵያውያን መካከል የአንደኛዋ ህይወት ማለፉ ታወቀ።
ባለትዳርና የሁለት ልጆች እናት የሆኑት ወ/ሮ አስሊ ኑሬ በደረሰባቸው ቃጠሎ ተገቢውን ህክምና ሳያገኙ በመቅረታቸው ማክሰኞ ጠዋት ህይወታቸው ማለፉን ለኢሳት ከደረሰው መረጃ ለማወቅ ተችሏል።
በቅርቡ ኦሮሚያ ከተካሄደው መጠነ ሰፊ ግድያ፣ ድብደባ፣ አፈናና እስራት ሸሽተው ግብጽ መድረሳቸው የተገለጸው እነዚህ ሁለት የኦሮሞ ተወላጅ የሆኑ ኢትዮጵያውያን፣ ራሳቸውን ያቃጠሉት በተቃውሞ መሆኑን ተመልክቷል።
ሁለቱ ኢትዮጵያውያን ራሳቸውን በማቃጠል ተቃውሟቸውን የገለጹት የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ኮሚሽን የካይሮ ቢሮ የስደተኝነት ጥያቄያቸው ውድቅ በማድረጉ እንደሆነም መዘገባችን ይታወሳል። ይኸው ቢሮ አሁንም ድረስ ለስደተኞቹ ተገቢ ምላሽ እንዳልሰጣቸው ለኢሳት የደረሰው መረጃ ያስረዳል።
በግብፅ ካይሮ የሚገኘው የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን በርካታ ኢትዮጵያውያን የጥገኝነት ጥያቄ ውድቅ በማድረጉ ብዙዎች በባህር ወደ አውሮፓ ለመሻገር በሚያደርጉት ጉዞ ህይወታቸው ማለፉ ይታወቃል።