በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሪዎስ የሚመራው ቅዱስ ሲኖዶስ የትግራይንና የጎንደርን ህዝብ ለማፋጀት የሚደረገው ሙከራ እንዲቆም ጥሪ አቀረበ

ኢሳት (ሃምሌ 18 ፥ 2008)

በፓትሪያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሪዎስ የሚመራው ቅዱስ ሲኖዶስ በወቅታዊ ሁኔታ ላይ ባወጣው መግለጫ የትግራይንና የጎንደርን ህዝብ ለማፋጀት የሚደረገው ሙከራ እንዲቆም ጥሪ አቀረበ። በኦሮሚያ ክልል በ400 ዜጎች ላይ የተፈጸመውን ግድያ በድጋሚ ያወገዘው የቅዱስ ሲኖዶስ መግለጫ ለሃገሪቱ ችግር መፍትሄ እንዲሰጥ ጥሪ አቅርቧል።

“ለሃያ አምስት ዓመት አንዱን ከሌላ ጋር በማጋጨትና በማጣላት ጊዜውን የሚያጠፋው ይህ መንግስት አሁንም በጥፋቱ ቀጥሎበት ይገኛል” ያለው የቅዱስ ሲኖዶስ መግለጫ ህዝብም ለነጻነቱ የራሱን አስተዋፅዖ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርቧል።

የ400 ኢትዮጵያውያን የኦሮሞ ተወላጆች የተገደሉበትን ድርጊት በማስታወስ እርምጃው ያወገዘው የቅዱስ ሲኖዶስ መግለጫ፣ በአዲስ አበባ ከተማ በቅርቡ ነዋሪዎችን በማፈናቀል የተካሄደውን ድርጊት ሃላፊነት ከሚሰማው መንግስት የማይጠበቅ ሲል ሲል ኮንኗል።

የወልቃይት የመብት ጥያቄን ተከትሎ የተነሳውንም መዝገብ በተመለከተ ቅዱስ ሲኖዶሱ በመግለጫው በዝርዝር ተመልክቷል። ኣሁን በጠመንጃ አፈሙዝ ምድርህን ልቀቅ የሚባለው የጎንደር ህዝብ ሆነ ታላቁ የትግራይ ህዝብ ለብዙ ሺህ ዓመታት በወንድማማችነት አብረው ኖረዋል የሚለው የቅዱስ ሲኖዶሱ መግለጫ “ለሃገሩ አንድነት ከኢትዮጵያውያን ወንድሞቹ ጋር ክቡር ዋጋ ሲከፍል የኖረውን የጎንደር ህዝብና ትውልድ ለማጥፋት በኢትዮጵያ ያለው መንግስት የሚፈጽመው ግፍና በደል ቅዱስ ሲኖዶሱን በእጅጉ አሳዝኖታል” በማለት የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ይህን ግፍና በደል ያስቆሙትም ዘንድ ጥሪ እናቀርባለን ብሏል።