በድሬዳዋ ከተማ በወባና ዳንጊ በሽታ በርካታ ሰዎችን እንደተጠቁ ተነገረ

ኢሳት (ሃምሌ 18 ፥ 2008)

በድሬዳዋ ከተማ የተከሰተን የወባና የዳንጊ ትኩሳት በሽታ ተከትሎ በየዕለቱ በትንሹ ስድስት ሰዎች ወደ ህክምና መስጫ ተቋማት በመግባት ላይ መሆናቸው ተገለጠ።

የክረምት ወቅቱን ተከትሎ በከተማዋና በዙሪያዋ ባሉ መንደሮች በመስፋፋት ላይ ያለውን የበሽታውን ስርጭት ለመቆጣጠር የመከላከሉ ስራ በዘመቻ እየተካሄደ መሆኑን የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ሰኞ አስታውቋል።

የተላላፊ በሽታዎችን ስርጭት በአጭር ጊዜ ለመቆጣጠር ሲባል ባለፉት ሁለት ሳምንታት ውስጥ 94ሺ ኬሚካል የተነከረ አጎበር ለነዋሪዎች መሰራጨቱንና ወደ 23ሺ በሚጠጉ መኖሪያ ቤቶች ላይ የጸረ-ወባ ኬሚካል ስርጭት መከናወኑን የከተማዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ መግልጹን በሃገር ውስጥ ያሉ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

ባለፉት ሁለት ሳምንታት በቀን በትንሹ ስድስት ሰዎች ለዳንጊ ትኩሳት በሽታ ህክምና ወደ ህክምና መስጫ ተቋማት በመግባት ላይ መሆናቸው ታውቋል።

በወባ ትንኝ አማካኝነት የሚተላለፈው የዳንጊ በሽታ ታማሚዎችን ለህመም በመዳረግ ለቢጫ ወባ በሽታ የማጋለጥ ሃይል እንዳለው የአለም ጤና ድርጅት መረጃ ያመለክታል።

በድሬዳዋ ከተማ ለሶስተኛ ጊዜ የተከሰተውን የዳንጊ በሽታ በቁጥጥር ስር ለማዋል የከተማዋ አስተዳደር የተለያዩ ርብርቦችን እያካሄደ እንደሚገኝ የድሬዳዋ ከተማ ከንቲባ አቶ ኢብራሂም ኡስማን ለመገናኛ ብዙሃን ገልጸዋል።

የክረምት ወቅት እየተጠናከረ በመሄዱ ምክንያት በተለያዩ ክልሎች ሊቀሰቀሱ ይችላሉ የሚል ስጋት መኖሩን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታውቋል።

በመዲናይቱ አዲስ አበባ ከተማ በመሰራጨት ላይ ያለውን የኮሌራ በሽታ ለመቆጣጠር ሚኒስቴሩ ከተለያዩ አለም አቀፍ ተቋማት ጋር በመተባበር ርብርብን እያካሄደ መሆኑን በድጋሚ ገልጿል።

እስካሁን ድረስ በትንሹ ለስድስት ሰዎች ሞት መንስዔ የሆነውን ይህንኑ የተላላፊ በሽታ ስርጭት ለመቆጣጠር ከ20 የሚበልጡ ጊዜያዊ የህክምና መስጫ ተቋማት አገልግሎትን እየሰጡ እንደሚገኝ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ይገልጻል።