ኢሳት (ሃምሌ 18 ፥ 2008)
በመንገባት ላይ ባለው የአባይ ግድብ ፕሮጄክት ከግብፅ ጋር አለመግባባት ውስጥ የምትገኘው ኢትዮጵያው ከግብፅ የሚገነቡ የመድሃኒት ምርቶችን አገደች።
የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በ11 ኩባንያዎች ላይ የተጣለው እገዳ የሃገሪቱን መስፈርት የማያሟሉ ሆነው ስላልተገኙ ነው ሲል ምላሽን መስጠቱን አል-ማስሪ የተሰኘ የግብፅ ጋዜጣ ዘግቧል።
በቅርቡ ወደ ግብጽ በመጓዝ በ13 የሃገሪቱ የመድሃኒት አምራት ፋብሪካዎች ላይ ጉብኝትን ያደረጉ የጤና ጥበቃ ተወካዮች 11ዱ ደረጃቸውን ያልጠበቁ ሆነው የተገኙ ናቸው ሲሉ በእገዳው ዙሪያ ምላሽ መስጠታቸው ታውቋል።
ይሁንና የመድሃኒት አምራቾችና ላኪዎች ምክር ቤት ሃላፊ የሆኑት ማጅድ ጂዮርጅ ኢትዮጵያ እገዳ የጣለችባቸው ኩባንያዎች ከ15 ሃገራት መድሃኒትን የሚያቀርቡ ተቋማት እንደሆኑ ለጋዜጣው ገልጸዋል።
ከኢትዮጵያ በኩል የቀረቡ ምክንያቶች በአግባቡ ለመመርመር የምክር ቤቱ አባላትን ጨምሮ በግብፅ የሚገኙ የኢትዮጵያ አምባሳደርን በማሳተፍ በጉዳዩ ዙሪያ አስቸኳይ ምክክር እንደሚካሄድ ሃላፊው አስታውቀዋል።
በርካታ የግብፅ መድሃኒት አምራች ኩባንያዎች የተለያዩ መድሃኒቶችን ለኢትዮጵያ ከአሰር አመት በላይ ሲያቀርቡ መቆየታቸው የታወቅ ሲሆን ሁለቱ ሃገራት በአባይ ግድብ ዙሪያ ያላቸው ልዩነት መፍትሄን ሳያገኝ በሌላ ጉዳይ አለመግባባታቸው ያላቸው ልዩነት ያሰፋዋል ተብሎ ተሰግቷል።
ኢትዮጵያ ከግብጽ ከምታስገባው መድሃኒት በተጨማሪ በርካታ የሃገሪቱ ኩባንያዎች መድሃኒትን ጨምሮ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ስራ ላይ በኢትዮጵያ ተሰማርተው እንደሚገኙ ለመረዳት ተችሏል።
እንደፈረንጆቹ 2013 ዓም ኢትዮጵያና ግብፅ የንግድ ልውውጣቸው ወደ 140 ሚሊዮን አካባቢ ደርሶ የነበር ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ድርሻ ወደ 30 ሚሊዮን ዶላር አካባቢ ብቻ መሆኑን ከኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ ያመለክታል። ባለፈው ወር የንግድ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር ስምምነትን አድርገው የነበሩት ሁለቱ ሃገራት የንግድ ልውውጡ ገቢን ወደ 200 ሚሊዮን ዶላር ለማድረስ ስምምነት ማድረጋቸው ይታወሳል።
ኢትዮጵያ ስጋን፣ ጥራጥሬን እንዲሁም የቁም እንስሳትና ቡናን ወደ ግብፅ የምትልክ ሲሆን ግብፅ በበኩሏ የተለያዩ መድሃኒቶችንና ኬሚካሎችን ለኢትዮጵያ በማቅረብ ላይ ትገኛለች።
በ11ዱ የመድሃኒት ኩባንያዎች ላይ የተጣለው እገዳ እስመቼ ድረስ የሚቆይ እንደሆ የተገለጸ ነገር የለም።