በአቶ ሃብታሙ አያሌው ሊሰጥ የነበረውን የህክምና ጥያቄ ብይን ለሶስተኛ ጊዜ አራዘመ

ኢሳት (ሃምሌ 15 ፥ 2008)

የፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከሃገር እንዳይወጣ እገዳ ተጥሎበት ለሚገኘው አቶ ሃብታሙ አያሌው አርብ ሊሰጥ የነበረውን ብይን ለሶስተኛ ጊዜ አራዘመ።

የአቶ ሃብታሙ ቤተሰቦች በህክምና የቦርድ አባላት የጸደቀን እና አቶ ሃብታሙ ከሃገር ውጭ እንዲታከሙ የተላለፈን የባለሙያዎች ውሳኔ ከፍርድ ቤት ቢያቀርቡም ፍ/ቤቱ የቀረበለትን ጥያቄ በአዲስ መልክ ለመመልከት ከቀጣዩ ሳምንት (ሃምሌ 19 ፥ 2008) ዓም ተለዋጭ ቀጠሮን እንደሰጠ ከሃገር ቤት የተገኘው መረጃ አመልክቷል።

ፍ/ቤቱ ከዚህ በፊት የቀረበለት ጥያቄ የተሟላ አይደለም ሲል የቀረበለትን ጥያቄ ሳይቀበል መቅረቱ የሚታወስ ሲሆን፣ ጉዳዩን ባለፈው ሳምንት የተመለከተው ፍርድ ቤቱ ዳኞች አልተሟሉም በማለት ውሳኔ ሳይሰጥ መቅረቱ ታውቋል።

በፅኑ ህመም ላይ የሚገኘው የአንድነት ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ሃብታሙ አያሌው ለህመሙ አፋጣኝ ህክምናን ካላገኘ በሽታው መልኩን እየቀየረ ሊሄድበትና አሳሳቢ መሆኑን ሃኪሞች በመግለጽ ላይ መሆናቸውን ለመረዳት ተችሏል።

የፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የፓርቲ አመራር የተጣለበት እገዳ እንዲነሳለት ለቀረበለት ጥያቄ የፊታችን ማክሰኞ ውሳኔን ያስተላልፋል ተብሎ ይጠበቃል።

አምነስቲ ኢንተርናሽናልን ጨምሮ የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት መንግስት የሰብዓዊ መብትን ግምት ውስጥ በማስገባት አቶ ሃብታሙ አያሌው ላይ የጣለውን እገዳ በአስቸኳይ እንዲያነሳ ጥያቄን እያቀረቡ ይገኛል።

አቶ ሃብታሙ በእስር ቤት እያለ የደረሰበት ኢሰብዓዊ ድርጊትና ስቃይ ለህመሙ ምክንያት መሆኑን አምነስቲ ኢንተርናሽናል ሃላፊዎች መግለጻቸው ይታወሳል።