ኢሳት ((ሃምሌ 12 ፥ 2008)
በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሃረርጌ ዞን በሚገኘው አሰቦት ከተማ የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች በአንድ ነዋሪ ላይ በፈጸሙት ድብደባ ተቃውሞን ቀስቅሶ በትንሹ 30 ሰዎች መታሰራቸውንና ድርጊቱ በአካባቢው ውጥረት ማንገሱን እማኞች ለኢሳት አስታወቁ።
የከተማዋ ነዋሪዎች በከተማው ከንቲባ ላይ ያላቸውን ተቃውሞና ቅሬታ ማክሰኞ መግለጽ በጀመሩበት ጊዜ የጸጥታ ሃይሎች አንድ ነዋሪን በጠመንጃ ስለት (ሳንጃ) ጭንቅላቱን እንደወጉትና ድርጊቱን ተጨማሪ ተቃውሞ መቀስቀሱን እማኞች ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ ገልጸዋል።
የጸጥታ ሃይሎች የወሰዱትን አሰቃቂ እርምጃ በአሰቦት ከተማ ነዋሪዎች ዘንድ ቁጣ መቀስቀሱን የተናገሩት እማኞች የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች ለተቃውሞ ከተሰባሰቡ ሰዎች መካከል ወደ 30 የሚደርሱ ነዋሪዎች ማሰራቸውን አክለው አስታውቀዋል።
በጸጥታ ሃይሎች የስለት ጥቃት የደረሰበት ግለሰብ በአሁኑ ሰዓት ለህይወቱ በሚያሰጋ ጉዳት በሆስፒታል ህክምና እየተደረገለት እንደሚገኝ ለደህንነታቸው ሲሉ ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ እማኞች አስረድተዋል።
በከተማዋ የተቀሰቀሰውን ተቃውሞ ተከትሎ በስፍራው የሚገኙ ፈጥኖ ደራሽ ሃይሎች የቤት ለቤት ፍተሻ ጭምርን በማካሄድ ነዋሪዎችን እያሰሩ መሆናቸውን ከእማኞች ለመረዳት ተችሏል።
ለእስር ከተዳረጉት ሰዎች በተጨማሪ በርካታ የአሰቦት ከተማ ነዋሪዎች በመንግስት የጸጥታ ሃይሎች ድብደባ እንደተፈጸመባቸው እማኞች የተጎዱ ግለሰቦችን ስም በመጥቀስ ለኢሳት አስረድተዋል።