ሐምሌ ፲፪ ( አሥራ ሁለት ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በምእራብ ሸዋ ጀልዱ ወረዳ በጃዊ ቦኒ ከተማ ከፍተኛ ህዝባዊ አመጽ በመካሄድ ላይ ሲሆን፣ ከተለያዩ የገጠር አካባቢዎች የተሰባሰቡ ነዋሪዎች መንገዶችን በመዝጋት እና ገዢውን ፓርቲ የሚያወግዙ መፈክሮችን በማሰማት ተቃውሞ እያደረጉ ነው። እስካሁን ባለው መረጃ 5 ሰዎች ቆስለዋል።
በምእራብ ሃረርጌ አሰቦት ወረዳም እንዲሁ ከፍተኛ ህዝባዊ አመጽ ተቀጣጥሎአል። ትናንት የጊንጪ ጀልዱ ግንደበረት መንገድ ሙሉ በሙሉ የተዘጋ ሲሆን ፣ ህዝቡ ወያኔ እንዳይኖር በአገራችን፣ ወያኔ እንዳይረግጥ መሬታችን፣ መንገድ እንዝጋ ተነሱ ሁላችን የሚል በኦሮምኛ እያዜመ አመጹን አቀጣጥሎአል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ ዓለማቀፍ ድጋፍ ሰጪ ቡድን መንግስት መብታቸውን በጠየቁ የጎንደር ነዋሪዎች ላይ ይወሰደውን የኃይል እርምጃ አውግዟል።
ዓለማቀፍ ድጋፍ ሰጪ ቡድኑ በጎንደር የተከሰተውን ቀውስና የተወሰደውን እርምጃ አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ የማንነት ጥያቄንም ይሁን ሌላ የመብት ጥያቄን በህጋዊና ህገ-መንግስታዊ መንገድ ብቻ መፍታት የሚገባው መንግስት ራሱ ህገ መንግስቱን በመጣስ ሀገሪቷን ወደ ቀውስ አስገብቷታል ብሏል። “በኦሮሞ አብዮት ወቅትም የታዬው ይኸው ነው” ያለው የኮንግረሱ መግለጫ፤ የራሱን ህግ ከማያከብር ህገ-ወጥ መንግስት መፍትሔ መጠበቅ አይቻልም ብሏል።
በመሆኑም መብቱን በጠዬቀው የጎንደር ሕዝብ ላይ እየተወሰደ ያለው የኃይል እርምጃ እንዲቆም አጥብቀን እንጠይቃለን ብሏል የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ ።
የመብት ጥያቄ በማንሳታቸውና ሀሳባቸውን በመግለጻቸው ሳቢያ ብቻ የታሰሩ የኃሊን እስረኞች እንዲፈቱ የጠዬቀው የኮንግረሱ ድጋፍ ሰጭ ቡድን፤ ባለፉት ስምንት ወራት ከመብት ጥያቄ ጋር በተያያዘ ስለተገደሉት ዜጎች ገለልተኛ አጣሪ አካል ተቋቁሞ ጉዳዩን እንዲያጣራ ሲል አሣስቧል።
“ለሃያ አምስት ዓመታት በሕዝባችን ጫንቃ ላይ የተንሰራፋውን ፋሽስታዊ አገዛዝ አሽቀንጥረን ለመጣል ፤በጋራ ታግለን ነጻነታችንንከማስከበር ውጪ አማራጭ የለንም”ሲልም ኮንግረሱ የመተባበርን አስፈላጊነት በአጽንዖት ገልጿል።
በመሆኑም መላው ህዝብ መብቱን ለማስከበር የሚያደርገውን ትግል በቅንጅት እንዲያደርግ የኮንግረሱ ድጋፍ ሰጪ ቡድን ጥሪውን አቅርቧል።