አቶ ሃብታሙ አያሌው ከሕክምና ቦርድ ማረጋገጫ ቢያገኝም ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ሳይሰጥ ቀረ

ሐምሌ  ፲፪ ( አሥራ ሁለት ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በከፍተኛ ሕመም የሚሰቃየው አቶ ሀብታሙ አያሌው ወደ ውጭ አገር ሄዶ ለመታከም የሚያስችለውን ተጨማሪ የሕክምና መረጃ ቦርድ እንዲያቀርብ በፍርድ ቤት ትእዛዝ ከተሰጠ በሁዋላ፣  የሕክምና ቦርድ አባላት የፈረሙበትና ታማሚው በግድ ወደ ውጭ ወጥቶ መታከም እንዳለበት የሚያረጋገጥ ማስረጃውን ይዞ ቢቀርብም የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞች አልተሰየሙም በሚል ምክንያት ቀጠሮዎችን በማጓተት ፍርድ ቤቱ ብይን ሳይሰጥ ቀርቷል።

ከሃብታሙ አያሌው ወዳጆችና ቤተሰቦች ”ለምን ይህ ሊሆን ቻለ?” ተብለው ለቀረበላቸው ጥያቄ ዳኛ ዳኜ መላኩ ሲመልሱ ”ዳኛ እንዲሰየም ለፍርድ ቤቱ ፕሬዚዳንት በማመልከቻ አቅርቡ” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። ሌሎች ዳኞች በበኩላቸው ”ዳኛ አልተሟላም፣ ቀሪው ዳኛ ደቡብ ክልል ቤተሰቦቹን ሊያመጣ ሄዷል፣ እስከ እርብ ይመጣል። ዳኛ ባይሟላ እንኳን እስከ አርብ ውሳኔ እንሰጣችኋለን። እየመጣችሁ ጠይቁን” የሚሉ ምላሾች ሰጥተዋል።

አቶ ሃብታሙ አያሌው እራሱን ስቶ ድጋሜ ወደ ሆስፒታል የገባ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ያለበት የጤንነት ሁኔታ አሳሳቢ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ታውቋል።