ሃምሌ 10 ቀን 2008 ዓም ብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎትና የፌደራል ፖሊስ የጋራ ጸረ ሽብር ግብረሃይል የተባለ ተቋም በሰሜን ጎንደር በመካሄድ ላይ ያለውን ህዝባዊ የመብት ትግል በሽብርተኝነት እና በዘር በመፈረጅ በህዝቡ ውስጥ ጥርጣሬ እንዲፈጠር ያደረገው ሙከራ አሳፋሪ ነው ሲሉ የኮሚቴ አባላቱ ለኢሳት ገልጸዋል።
ለጊዜው ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁት የኮሚቴው ከፍተኛ አመራር፣ አንድ አገርን እመራለሁ የሚል ፓርቲ ከሜዳ ተነስቶ የህወሃትን አመለካከቱ ማንጸባረቁ የወልቃይት ጠገዴን ህዝብ አእምሮ አድምቶታል ብለዋል።
“እነሱ ላለፉት 40 አመታት ህዝባችንን ሲያፍኑ የቆዩ በመሆኑ አሁን የሚሉት ብዙም አይገረመኝም” ያሉት የኮሚቴው አባል፣ ዛሬ ሰሜን ጎንደር መስተዳደር ሄደን እንዲህ አይነቱ የቅስቀሳ ወረርሽኝ እንዲቆም በጠየቅነው መሰረት ማስተባበያ እንደሚሰጥ ቃል ተገብቶልናል ብለዋል።
ጥያቄያችንን በሃይል ለማፈን ሲመጡ አስፈላጊውን መልስ ሰጥተናል ያሉት የኮሚቴው አባል፣ ተመሳሳይ አፈና እናካሂዳለን ካሉ ከህዝባችን ጋር በመሆን በቀጣይም እርምጃ እንወስድባቸዋለን ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
በአሁኑ ሰአት ከሰሜን ጎንደር ውጭ በአዲስ አበባ የሚገኙ የወልቃይት ተወላጆችም እየታሰሩ ነው ያሉት የኮሚቴው አባል፣ ከዚህ ቀደም ሶስት ወጣቶችን አሰልፈው ከኤርትራ እንደመጡ አድርገው ድራማ ለመስራት ሲሉ ድራማውን እንደሲራ የታዘዘው ወጣት መሳሪያውን እንደያዘው እንደተፋባቸው፣ ሁለቱን ወጣቶች ደግሞ ወደ ባንክ ቤት ወስደው ዝረፊያ ሊፈጽሙ እንደነበር እንዲናገሩ ሲያስገድዱዋቸው ወጣቶቹ እኛ ኤርትራ አልሄድንም፣ በህዝባችንም ላይ እንዲህ አይነት ስራ አንሰራም ማለታቸውን በማስታወስ፣ አሁን የጸረ ሽብር ግብረሃይል የሰራው ሁሉ ድራማ ነው ብለዋል
“ከትግራይ ህዝብ ጋር ተዋልደናል ተጋብተናል የሚሉት የኮሚቴው አባል ፣ ጸባችን ከህወሃት አገዛዝ ጋር እንጅ ከህዝብ ጋር አይደለም “ ብለዋል።
በሌላ በኩል በጎንደር ከተማ አሁንም ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የሰራዊት አባላት ተመድበው በህዝቡ ላይ ጫና ለማሳደር እየሞከሩ ነው።
ኮ/ል ደመቀ ዘውዱ በጎንደር ማረሚያ ቤት ከቤተሰቦቻቸው ጋር የሚገኙ ሲሆን፣ እርሳቸውን ወደ ትግራይ ወይም ወደ ሌላ አካባቢ ለመውሰድ የሚደረገው ሙከራ ከፍተኛ ዋጋ ያስከፍላል ሲሉ የኮሚቴ አባላቱ በማስጠንቀቅ ላይ
ናቸው።