የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የሪዮ ኦሎምፒክን የሚወክሉ 43 አትሌቶች መረጠ

ኢሳት (ሃምሌ 8 ፥ 2008)

ከአንጋፋ የኢትዮጵያ አትሌቶች ቅሬታ ሲቀርብለት የቆየው የኢትዮጵያ አትሌትክስ ፌዴሬሽን ሀገሪቱን ከአንድ ወር በኋላ በብራዚል የሪዮ ኦሎምፒክ የሚወክሉ 43 አትሌቶችን መረጠ።

ተቃውሞን አስነስቶ በነበረው የማራቶን ዉድድር ዘርፍ በወንዶች አትሌት ለሚ ብርሃኑ ፣ ተስፋዬ ብርሃኑ፣ እና ተስፋዬ አበራ  የተመረጡ ሲሆን አትሌት ፈይሳ ሌሊሳ ዴሲሳ በተጠባባቂነት ተይዘዋል።

በማራቶን ውድድር በመጀመሪያዉ ዙር በተጠባባቂነት ተይዞ የነበረዉና ተቃዉሞን ሲያቀርብ የቆየዉ አትሌት ቀነኒሳ በቀለ ከውድድሩ ውጪ መሆኑን ታዉቋል።

አትሌት ቀነኒሳ በቀለና ሌሎች ታዋቂ ስፖርተኞች ለኦሎምፒክ ዉድድር በቂ ዝግጅት ሲያደርጉ ቆይተዉ በተሳታፊነት አለመያዛቸዉ ስነ-ልቦናዊ ጫናን እንዳሳደረባችዉ ሲገልፁ መሰንበታቸዉ የሚታወስ ነዉ።

ከአትሌቶቹ የቀረበን ቅሬታ እንደሚመለከት ሲገልፅ የቆየዉ የኢትዮጵያ አትሌትክስ ፌዴሬሽን በማጠቃለያ ምርጫዉ አትሌት ቀነኒሳ በቀለን ከኦሎምፒክ ውድድር አሰናብቷል።

አትሌት ቀነኒሳ በቀለን ጨምሮ 12 ታዋቂ አትሌቶች ፊዴሬሽኑ ያካሄደዉ ምርጫ ሀገርን ለመጥቀም ሳይሆን ግለሰቦችን ለመጥቀም የታሰበ ነዉ ሲሉ ተቃዉምን እያቀረቡ ይገኛሉ።

በሴቶች ማራቶን አትሌት ትዕግስት ቱፋ ፣ ማሬ ዲባባ፣ እና ትርፌ ፀጋዬ የተመረጡ ሲሆን አትሌት አበሩ ከበደ በተጠባባቂነት ተይዛለች።

አዳዲስ አትሌቶች በተካተቱበት የ 10ሺ ሜትር የውድድር ዘርፍ አትሌት ይግረም ደመላሽ ፣ ታምራት ቶላ ፣ እና አትሌት አባዲ ሃዲስ ኢትዮጵያን በመወከል በሪዮ ተሳታፊ እንደሚሆኑ ለመረዳት ተችሏል።

በሴቶች 10ሺ ሜትር አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ ፣ ገለቴ ቡርቃና፣ አልማዝ አያና የተመረጡ ሲሆን አትሌት ነፃነት ጉደታ በተጠባባቂነት ተይዛለች።

በብራዚል ኦሎምፒክ ከ40 በላይ አትሌቶችን የምታሳትፈዉ ኢትዮጵያ በማራቶን ፣ በ10 ሺ ፣ በ5 ሺ ፣ በ800 ሜትር ፣ በ 1ሺ 500 ፣ በ3 ሺ መሰናክል በሁለቱም ጾታዎች ተሳታፊ እንደምትሆን ታዉቋል።