ኢሳት (ሃምሌ 8 ፥ 2008)
በኢትዮጵያና የኤርትራ ድንበር አካባቢ ስላሉ በኢትዮጵያ ወታደሮች እንቅስቃሴ ለኤርትራ መንግስት መረጃን ሲያቀብሉ ነበሩ የተባሉ ዘጠኝ ግለሰቦች ከ3 ወር እስከ 4 ዓመት በሚደርስ እስራት ተቀጡ ።
ቅጣቱ ከተላለፈባቸዉ መካከል አምስቱ ኤርትራውያን መሆናቸዉንና ከ2004 ዓም እስከ 2006 ዓም ባሉት ጊዚያት ዉስጥ ከኤርትራ የመረጃ ሰራተኞች ጋር ሚስጢራዊ ግንጙነት በመፍጠር የስለላ ድርጊት ሲፈፅሙ መቆየታቸዉን የመንግስት መገናኛ ብዙሃን አርብ ዘግበዋል።
የሀገሬቱ ሚስጥራዊ መረጃ በማቀበልና በስለላ ወንጀል ክስ ተመስርቶባቸዉ የነበሩት ግለሰቦች በቀረበባቸው ክስ ጥፋተኛ ሆነዉ በመገኘታቸዉ ከ3 ወር እስከ 4 ዓመት የሚደርስ ቅጣት ተላልፎባቸዋል።
የቀረበባቸዉ ክስ አስተባብለዉ ሲከራከሩ ነበር የተባሉት ዘጠኙ ኢትዮጵያና ኤርትራዉያን የተለያዩ መሳሪያዋችን ለነዋሪዎች ሲሸጡ እንደነበር ከቀረበባቸዉ ክስ ለመረዳት ተችሏል።
ግለሰቦቹ ለሁለት ዓመታት ያህል ጊዜ የስለላ ድርጊትን ሲፈፅሙ ቆይተዋል ቢባልም መቼና የት በቁጥጥር ስር እንደዋሉ የተገለፀ ነገር የሌለ ሲሆን ሁሉም ተከሳሾች ለ5 ዓመት ከማነኛዉም ህዝባዊ መብታቸዉ እንዲታገዱ ፍርድ ቤቱ ዉሳኔ መስጠቱን ከሀገር ቤት የተገኘዉ መረጃ አመላክቷል።