ኢሳት (ሃምሌ 8 ፥ 2008)
በኢትዮጵያ በድርቅ በተጎዱ አካባቢዎች ባለፉት ስድስት ወራት የተወለዱ ከ300 ሺ በላይ ህፃናት በአስከፊ የምግብ እጥረት ውስጥ መሆናቸዉን የካናዳ የክርስቲያን ችልድረንስ ፈንድ ገለጠ ።
ድርቁ በህፃናትና በነፍሰ ጡር እናቶች ላይ ከፍተኛ ጉዳትን እያደረሰ እንደሚገኝ ያስታወቀዉ ድርጅቱ፣ አዲስ የተወለዱት ህፃናት አፋጣኝ እርዳታን ካላገኙ ህይወታቸዉ አደጋ ውስጥ እንደሚሆን አሳስቧል።
ድርቅ ጉዳት እየደረሰባቸዉ ባሉት አካባቢዎች ባሉበት ስድስት ወራቶች ውስጥ ብቻ 350 ሺ ህፃናት የተወለዱ ሲሆን ህፃናቱና እናቶቻቸዉ በከፋ የምግብ እጥረት ውስጥ መሆናቸውን የካናዳ የክርስቲያን ችልድረንስ ፈንድ ሀላፊ የሆኑት ማርክ ሉኩዉስኪ ገልፀዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅትና ሌሎች አለም አቀፍ ተቋማት ለአስቸኳይ የምግብ እጥረት ተጋልጠዉ ለሚገኙ ከ10 ሚሊዮን ሰዎች መካክል ወደ ስድስት ሚሊዮን የሚሆኑት ህፃናት መሆናቸውን በመግለፅ ላይ ናቸዉ።
ወደ 6 ሚሊዮን አካባቢ ለሚደርሱት ህፃናት መካከል ግማሽ ሚሊዮን የሚሆኑት ለከፋ የምግብ እጥረት በመጋለጣቸዉ ምክንያት የጤናና የአካል ጉዳት እየደረሰባቸዉ እንደሆነ ታውቋል።
የሀፃናቱን ህይወት ለመታደግ የካናዳዉ የህፃናት መርጃ ድርጅት ለሌሎች አካላት ጋር በመሆን የእርዳታ አቅርቦት እያደረገ እንደሚገኝ የካናዳ የክርስቲያን ችልድረንስ ሃላፊ የሆኑት ማርክ ሉኩዉስኪ ገልፀዋል።
በሀገሪቱ ለምግብ ድጋፍ ለተጋለጡ ሰዎች የሚያስፈልገው እረዳታ ርብርብን እንደሚያስፈልገዉ የተናገሩት ሀላፊዉ በተለይ ህፃናቱን በህይወት ለማቆየት የሚደረገዉ ጥረት ቅድሚያ ትኩረትን የሚሻ እንደሆነ አስረድተዋል።
በዚሁ ድርቅ ዙሪያ ሪፖርቱን ያቀረበዉ ዋሽንግተን ፖስት ጋዜጣ የካናዳዉ የህፃናት መርጃ ተቋም ለአርሶ አደሮች የዘር እህልን እና ሌሎች ድጋፍን ለማቅርብ ጥረት በማድረግ ላይ መሆኑን ዘግቧል።