ኢሳት (ሃምሌ 8 ፥ 2008)
በግብፅ ፓርላማ የመከላከያና የደህንነት ጉዳዮች ኮሚቴና የፓርላማ አባል ሃገሪቱ ከኢትዮጵያ ጋር በአባይ ግድብ ዙሪያ ያላትን ልዩነት በወታደራዊ እርምጃ ብቻ የሚፈታ ነው ሲሉ ማሳሰባቸውን የግብፅ መገናኛ ብዙሃን አርብ ዘገቡ። የፓርላማ አባሉ አህመድ ኢስማዔል የእስራዔሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔትኒያሁ በቅርቡ በኢትዮጵያ ያደረጉት ጉብኝት የአባይ ወንዝ በተዘዋዋሪነት ለመቆጣጠር ያለመ እንደሆነ ገልጸዋል።
በግብፅ ፓርላማ የሃገሪቱን የመከላከያና የብሄራዊ ደህንነት ጉዳዮች የሚከታተለው ኮሚቴ አባል የሆኑት አህመድ ኢስማዔል ሃገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ችግር ለመፍታት ወታደራዊ ዕርምጃ ብቻ መፍትሄ መሆኑን ይፋ እንዳደረጉ ማዳ ማስር የተሰኘ የግብፅ የመገናኛ ብዙሃን ተቋም ዘግቧል።
የግብፅ ባለስልጣናት በበኩላቸው በሁለቱ ሃገራት መካከል እየሰፋ የመጣውን ልዩነት ለመመከት የሁለቱ ሃገራት ባለስልጣናት በርዋንዳ እየተካሄደ ባለው የአፍሪካ መሪዎች ልዩ ጉባዔ ላይ እንደሚመክሩ አስታውቀዋል።
ኢትዮጵያና ግብጽ ሁለት የፈረንሳይ ኩባንያዎችን በመምረጥ የአባይ ግድብ ግንባታ የታችኛው የተፋሰሱ (በተለይ በግብፅ ላይ) የሚያመጣውን ተፅዕኖ ለማስጠናት ስምምነት ቢደርሱም እስካሁን ድረስ ከኩባንያዎቹ ጋር ሳይፈራረሙ ቀርተዋል።
የሁለቱ ሃገራት ልዩነት እየሰፋ በመጣበት በዚሁ ወቅት የግብፁ የፓርላማና የደህንነት ኮሚቴ አባል ሃገራቸው ወታደራዊ አማራጭን በብቸኝነት እንድትከተል ሃሳብን አቅርበዋል።
ከቀናት በፊት በኢትዮጵያ ጉብኝት ያደረጉት የእስራዔሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታኒያሁ ጉዳይ ከግብፅ ልዩ ትኩረትና ስጋት እየሆነ መምጣቱን ከካይሮ ዩኒቨርስቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር የሆኑት ታሪክ ፋህሚ ለግብፅ መገናኛ ብዙሃን ገልጸዋል።
የሃገሪቱ የቀድሞው የመስኖና የውሃ ሚኒስትር የነበሩት ሞሃመድ ናስር በበኩላቸው የአባይ ግድብ ግንባታ ያመጣውን ችግር ለመቅረፍ ግልፅ የሆነ መርሃ ግብር መከተል እንደሚገባ አሳስበዋል።
የሃገሪቱ የውሃ እና የመስኖ ልማት ሚኒስትር ሞሃመድ አብደል አቲ የኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን መሪዎች ከቀናት በኋላ በርዋንዳ እየተካሄደ ባለው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ ወቅት ከፈረንሳይ ኩባንያዎች ጋር ስምምነትን ይፈርማሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ አስረድተዋል።
በሁለቱ ሃገራት መካክል ከአራት አመት ያህል ጊዜ ሲካሄድ የቆየው ድርድር አልባት አለማግኘቱ ይታወቃል።