ኢሳት (ሃምሌ 7 ፥ 2008)
የአሜሪካ መንግስትን ጨምሮ የተለያዩ ሀገራት ዜጎቻቸዉ ወደ ጎንደር ከተማ እና አካባቢዉ በሚያደርጉት ጉዞ ላይ የጥንቃቄ እርምጃዎችን እንዲወስዱ አሳሰቡ።
አዲስ አበባ የሚገኘዉ የአሜሪካ ኤምባሲዉ ባልደረቦች ወደ ጎንደር ከተማ የሚያደርጉትን ጉዞ ለጊዜዉ እንዲያቋርጡ ያሳሰበ ሲሆን ዜጎቹም ወደ ጎንደር ከተማ በሚያደርጉት ጉዞ ላይ የጥንቃቄ እርምጃን እንዲያደርጉ ባሰራጭው መልእክት አመልክቷል።
አሜሪካዊያን ወደ ስፍራዉ ለሚያደርጉት የጉዞ ጥንቃቄ በተጨማሪ ላማንኛዉም ህዝባዊ ሰልፎችና ስብሰባዎች ራሳቸዉን እንዲያያገሉ ኤምባሲዉ አክሎ ጠይቋል።
ከአሜሪካ መንግስት በተጨማሪ የብሪታንያና የካናዳ መንግስታት ዜጎቻቸዉ ወደ ጎንደር ከተማ በሚያደርጉት ጉዞ ላይ ተመሳሳይ ጥንቃቄን እንዲያያደርጉ አሳስበዋል።
የብሪታንያ መንግስት ለዜጎቹ ባሰራጨዉ የማሳሰቢያ መልእክቱ በጎንደር ከተማ ያለዉ የፀጥታ ሁኔታ እጅጉን አሳሳቢ ሆኖ መቀጠሉን በመግለፅ በከተማዋ የተኩስ ልዉዉጦችና ሁከት መኖሩን አስታዉቋል።
በተመሳሳይ ሁኔታ የካናዳ መንግስት ዜጎቹን በኢትዮጵያ የሰሜን ግዛት አካባቢ በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ላይ ጥንቃቄን እንዲያደርጉ ለዜጎቹ ባሰራጨዉ መልዕክት ጠይቋል።
ከተለያዩ ሀገራት በተጨማሪ መቀመጫቸዉን በአዲስ አበባ ያደረጉ የተለያዩ አለም አቀፍ ድርጅቶችና ተቋማት ለሰራተኞቻቸዉ የጥንቃቄ መልዕክትን እያሰራጩ እንደሚገኝ ከሀገር ቤት ከተገኘ መረጃ በመረዳት ተችሏል።
ሐሙስ ከጎንደር ከተማ ዉጭ ባሉ አካባቢዎች በመካሄድ ላይ ያለዉ ተቃዉሞና ግጭት ቁጥሩ በትክክል ሊታወቅ ላልቻለ ሰዉ ሞት ምክንያት መሆኑን እማኞች ለኢሳት በመግለፅ ላይ ናቸዉ።
የፌደራል ፖሊስ በሰሜን ጎንደር ዙሪያ የፀጥታ ችገር እንዳለ ከቀናት በፊት ቢያረጋግጥም በጎንደር ከተማና አካባቢዉ እየተካሄደ ስላለዉ ግጭትም ሆነ ስለደረሰዉ ጉዳት የሰጠዉ ዝርዝር መረጃ የለም ።