ለቤተ-እስራዔላውያን የበጎ አገልግሎትን ሲሰጡ የነበሩ ድርጅቶች በጎንደር አየር ማረፊያ እንዲጠለሉ ተደረገ

ኢሳት (ሃምሌ 7 ፥ 2008)

ሰሞኑን በጎንደር ከተማ የተቀሰቀሰውን ግጭት ተከትሎ የእስራዔል መንግስት በአካባቢው ተሰማርተው የሚገኙ የበጎ አገልግሎት አባላትን ወደ አየር ማረፊያ ማስጠለሉን የሃገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ሃሙስ ዘገቡ።

የእስራዔል የበጎ አገልግሎት አባላት በጎንደር ከተማና ዙሪያ ከሚገኙ የቤተ-እስራዔላውያን የተለያዩ አገልግሎትን ሲሰጡ የነበሩ እንደሆነ ታውቋል።

ይሁንና ከቀናት በፊት በጎንደር ከተማ የተቀሰቀሰው ግጭት ለበጎ አገልግሎት አባላቱ ስጋት እየሆነ በመምጣቱ የእስራዔል ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቁጥራቸው በትክክል ያልታወቀውን አባላት ወደ አየር ማረፊያ ማስጠለሉ ተገልጿል።

የእስራዔል ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ የሆኑት ኢማኑዔል ናችሽን እስራዔላዊያኑ ከሰሜኑ የሃገሪቱ ክፍል ለቀው እንዲወጡ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ለእስራዔል መገናኛ ብዙሃን አስታውቀዋል።

ከተለያዩ ሃገራት የተውጣቱና በጎንደር ከተማ አገልግሎትን እየሰጡ የነበሩት እስራዔላውያን በአካባቢው በእርሻ፣ ትምህርትና ጤና ዙሪያ የተለያዩ ድጋፎችን ሲሰጡ እንደነበር ቃለ-አቀባዩ አስረድተዋል።

በቅርቡ በኢትዮጵያ ጉብኝትን ያደረጉት የእስራዔሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታኒያሁ በአዲስ አበባ እና ጎንደር ከተማ ወደ እስራዔል ለመጓዝ ለአመታት በመጠባበቅ ላይ የነበሩ ወደ 9 ሺ አካባቢ ቤተ እስራዔላውያን በቅርቡ እንደሚጓጓዙ መግለጻቸው ይታወሳል።

ሰሞኑን በጎንደር ከተማና አካባቢዋ የተቀሰቀሰውና ዕልባትን ያላገኘው ይኸው ግጭት ለቤተ እስራዔላውያኑ የደህንነት ስጋት እየሆነ መምጣቱን የእስራዔል መንግስት በመግለጽ ላይ ሲሆን፣ የተለያዩ ሃገራትም ዜጎቻቸው ወደ አካባቢው እንዳይጉዙ ማሳሰብያን እያወጡ ይገኛሉ።