ኢሳት (ሃምሌ 6 ፥ 2008)
የኬንያ መንግስት ባለፈዉ ሳምንት ከኢትዮጵያ ጋር የነዳጅ ማስተላለፊያ መስመር ለመገንባት ስምምነት መፈረሙን ቢገልፅም ኢትዮጵያ ከሀገሪቱ ጋር የተደረሰ ስምምነት የለም ስትል ማስተባበሏን የኬንያ መገናኛ ብዙሃን ረቡዕ ዘገቡ።
ከኢትዮጵያ በኩል የተሰጠዉ ይኸዉ ማስተባበያ የኬንያ መንግስት ይፋ ካደረገዉ መግለጫ ጋር የሚጋጭ መሆኑን ዴይሊ ኔሽን የተሰኘ የኬንያ ጋዜጣ ዘግቧል።
የኢትዮጵያ ጠ/ሚኒስተር አቶ ሀይለማሪያም ደሳለኝ ባለፈዉ ሳምንት በኬንያ ጉብኝት ባደረጉበት ጊዜ የኬንያ መንግስት የነዳጅ መስመሩን ለመገንባት ስምምነት ተደርሷል ሲል ይፋዊ መግላጫ ሰጥቶ እንደነበረ ጋዜጣዉ በጉዳዩ ዙሪያ ባቀረበዉ ሪፖርት አስታዉቋል።
ይሁንና የኢትዬጵያ የማዕድን ፣ ነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስተር ስምምነት ተደርሷል የተባለዉ መረጃ የተሳሳተ መሆኑን በመግለፅ ጉዳዩን አስተባብሏል።
ሚንስተሩ በሀሳብ ደረጃ የቀረበዉን የዚሁኑ የነዳጅ ማስተላለፊያ መስመር ግንባታ ለመመርመር እና አዋጭነቱን ለማየት ጊዜ ወሰዶ ለማጥናት ፍላጎት ማሳየቱን አስታዉቋል።
ሁለቱ ሀገራት ተሰማምተዋል ተብሎ የነበረዉ ፐሮጀክት ለኬንያዊ የላሙ ከተማ እስከ አዲስ አበባ ድረስ የሚዘልቅ የነዳጅ ማስተላለፊያ መስመር ለመገንባት እቅድ የነበረዉ እንደሆነ ታዉቋል።
የኬንያ መንግስት በፕሮጀክቱ ከኢትዬጵያ ጋር ለመስራት አዲስ እቅድን የያዘዉ ዩጋንዳ ከኬንያ ጋር የነበራትን ተመሳሳይ እቅድ በመሰረዝ ታንዛንያን በአማራጭነት ማየት ከጀመረች በኋላ መሆኑን በርካታ አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን መዘጋባቸዉ የሚታወስ ነዉ።
ተደርሷል በተባለዉ ስምምነት ወቅት የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚንስተር አቶ ሀይለማሪያም ደሳለኝ ፕሮጀክቱን እዉን ለማድረግ የሁለቱ ሀገራት ሚኒስተሮች በአመት ሁለት ጊዜ እየተገናኙ እንደሚወያዩ ገልፀዉ እንደነበር ሱዳን ትሪቢዩን ጋዜጣ ዘግቧል።
የዚሁኑ ግዙፍ ፕሮጀክት እዉን ማድረግ ኢትዬጵያ ቅድሚያ ሰጥታ የምትከታተለዉ ጉዳይ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅቱ ለመገናኛ ብዙሃን ገልፀዉ እንደነበር ለመርዳት ተችሏል።
ይሁንና የኢትዬጵያ ባለስልጣናት ከቀናት በፊት ስምምነት አለመፈረሙን ማስተባበያ መስጠታቸዉ በበርካታ የኬንያ መገናኛ በዙሃን ዘንድ መነጋገሪያ ሆኖ ይገኛል።