ኢሳት (ሃምሌ 6 ፥ 2008)
የኢትዮጵያ መንግስት የማህበራዊ ድረ-ገጾች መዝጋቱን ተከትሎ የንግድ ድርጅቶች፣ የጋዜጠኞች፣ የአለም አቀፍ ተቋማት፣ የኢምባሲዎችና የኢትዮጵያውያን የዕለት ተዕለት ስራ መስተጓጎሉ ተነገረ።
ይህ በኢትዮጵያ መንግስት የተደረገው የማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን መዘጋት፣ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ፈተና እስኪጨርሱ ድረስ ብቻ የሚቆይ ነው ቢባልም፣ የማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን መዘጋት በእያንዳንዱ የማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን ተጠቃሚ ላይ ተጽዕኖ እንዳሳደረ ለማወቅ ተችሏል።
የግል ንግድ ድርጅቶች፣ የግል መስሪያ ቤቶች፣ ጋዜጠኞች፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች፣ ግለሰቦች፣ እንዲሁም የአለም አቀፍ ድርጅቶች በዚሁ በድረገጾች የአፈና ድርጊት የተነሳ የዕለት ተዕለት ግንኙነታቸው ተስተጓጉሎ እንደሚገኝና ለከፍተኛ ችግር እንደተዳረጉ ለማወቅ ተችሏል። እንዲህ አይነት የአፈና ድርጊት ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለው ተግባር እንደሆነ አክሰስ ናው (Access Now) የተባለ ድርጅት ሃላፊ ዴጂ ኦሉኮቱን (Deji Olukotun) ኳርትዝ አፍሪካ ለተባለ ጋዜጣ መናገራቸው ተመልክቷል።
በኢትዮጵያ የማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን ተጠቃሚነትና በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ በመምጣቱና ለሰብዓዊ መብት ጥበቃ (አድቦኬሲ) አገልግሎት በስፋት እየዋለ በመምጣቱ የኢትዮጵያ መንግስትን ከፍተኛ ስጋት ውስጥ ሳይጥለው እንዳልቀረ ይኸው ኳርትዝ አፍሪካ የተባለ ጋዜጣ በዛሬው እትሙ ዘግቧል።
ኢትዮጵያ ከዚህ በፊት ስካይፕን ጨምሮ የተለያዩ ድረገጾች የተጠቀሙ ዜጎች በ15 አመት እስር ይቀጣሉ ብላ እንደነበር በማስታወስ፣ የአሁኑ ድርጊትም ከ 12ኛ ክፍል ፈተና ጋር የተያያዘ ሳይሆን ተቃውሞዎችን ለማፈንና የድምፅና ስዕል ልውውጥን ለመቆጣጠር የተወሰደ ድርጊት ሊሆን እንደሚችል የፖለቲካ ተንታኞችና የማህበራዊ ሳይንስ ባለሙያዎች ይናገራሉ።
የኢንተርኔት አጠቃቀም ህግ በአገሪቱ ያሉትን የመንግስት ተቃዋሚዎችን፣ ጋዜጠኞችን እና የድረ-ገጽ ተጠቃሚዎችን ድምፅ ለማፈን ሆን ተብሎ የታቀደ ህግ እንደሆነ የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ይናገራሉ። የአሁኑ የኢትዮጵያ መንግስት ድርጊትም በመንግስት የሚወሰዱ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በእነዚሁ ማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን ለህዝብ ይፋ እየሆኑ በማስቸግሩ እንደሆነ እነዚሁ ተንታኞች ይናገራሉ።
ኢትዮጵያ ከዚህ በፊት በተለያዩ ጊዜያት የመገናኛ ብዙሃን የመረጃና ነጻነት ህግ እና የጸረ ሽብር ህግ ያጸደቀች ሲሆን፣ የህጎቹ አላማም ማህበረሰቡን በማስፈራራት የመረጃ ልውውጥን ማገድ እንደሆነ ይታወሳል።