ኢሳት (ሃምሌ 6 ፥ 2008)
ባሳለፍነው እሁድ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የተበረከተላቸውን የክብር ዶክትሬት ዲግሪ የተቀበሉት የማላዊ ፕሬዚደንት ፒተር ሙታሪካ ወደ ኢትዮጵያ ለመጓዝ የመንግስትን ገንዘብ አባክነዋል ተብለው ከፍተኛ ተቃውሞ ቀረበባቸው።
ባለፈው ዕሁድ ወደ ኢትዮጵያ ተጉዘው የነበሩት ፕሬዚደንቱ ለጉዞአቸው አንድ የደቡብ አፍሪካ የግል አውሮፕላንን እንደተከራዩና ከፍተኛ የመንግስት ገንዘብ አባክነዋል ተብለው ተቃውሞ እየቀረበባቸው መሆኑን የሃገሪቱ ኒያሳ ታይምስ የተሰኘ ጋዜጣ ዘግቧል።
ፕሬዚደንቱ የክብር ዶክትሬት ዲግሪያቸውን ተቀብለው ቢመለሱም የማላዊ ተቃዋሚ ፓርቲዎችና ታዋቂ ግለሰቦች ሃገሪቱ በከፍተኛ ድህነት ውስጥ እያለች ሙታሪካ የግል አውሮፕላን ተከራይተው ወደ ኢትዮጵያ መጓዛቸው ተገቢ አለመሆኑን ገልጸዋል።
በማላዊ የቻንስለር ኮሌጅ ዩኒቨርስቲ መምህር የሆኑት ሙስጠፋ ሁሴን ፕሬዚደንቱ የክብር ዶክትሬት ዲግሪያቸውን በመቀበል የወሰዱት እርምጃ እጅጉን አሳዛኝ ነው ሲሉ ለጋዜጣው ተናግረዋል።
የማላዊ ፕሬዚደንት ቀድሞ የነበራቸውን ተግባር ግምት ውስጥ በመክተት ለግላቸው የቀረበላቸውን የክብር ዶክትሬት ለመቀበል ከአራት ሰዓት ጉዞ የግል አውሮፕላን መከራየታቸው ተገቢ አይደለም ሲሉ የዩኒቨርስቲው መምህር አክለው ገልጸዋል።
የተበረከተላቸው የክብር ዶክትሬት ፕሬዚደንቱ ለሃገራቸው ሲነግሩት ከነበረው አመለካከት ጋር የሚጻረር እንደሆነም መምህሩ ለፕሬዚደንት ሙታሪካ የቀረበውን የክብር ዶክትሬት ተችተዋል።
የማላዊ ተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች በበኩላቸው ፕሬዚደንቱ ለግላቸው የተሰጠን የክብር ዶክትሬት ለመቀበል የመንግስት ገንዘብ ማባከናቸው ተገቢ አይደለም ሲሉ ተቃውሞ እያቀረቡ መሆኑ ኒያሳ ታይምስ ጋዜጣ በዘገባው አመልክቷል።
የማላዊ የማስታወቂያ ሚኒስቴር የሆኑት ፓትሪሺያ ካሊያቲ ፕሬዚደንቱ በግል አውሮፕላን ስለመጓዛቸው መረጃ እንደሌላቸው ምላሽን የሰጡ ሲሆን፣ የሃገሪቱ የፋይናንስ ሚኒስቴር ባለስልጣናት ሙታሪካ በኢኮኖሚ ክላስ መጓዝ የለባቸውም ሲሉ እንደነበር ለመረዳት ተችሏል።
የማላዊ የፋይናንስ መስሪያ ቤት ፕሬዚደንቱ በውድ የቲኬት ወጪ ጉዞ ማድረግ የለባቸውም ሲል ቢቆይም ሙታሪካ ንብረትነቱ የደቡብ አፍሪካ የሆነ የግል አውሮፕላን በመከራየት ወደ አዲስ አበባ መጓዛቸው እንደተረጋገጠ የሃገሪቱ መገናኛ ብዙሃን በመዘግብ ላይ ናቸው።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ባለፈው ዕሁድ ፕሬዚደንቱ አበርክተዋል ላለው የላቀ የትምህርት አስተዋጽዖ የክብር ዶክትሬት ማበርከቱ ይታወሳል።