በጎንደር የተነሳው ህዝባዊ ተቃውሞ ለሁለተኛ ቀን ሲካሄድ ዋለ

ሐም ( ስድስት ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የወልቃይት ጠገዴ የአማራ ማንነት ጥያቄ የኮሚቴ አባላትን ለመያዝ የህወሃት የደህንነት አባላት ጎንደር ከገቡ በሁዋላ፣ ከኮሚቴ አባላቱ መካከል አንዱ የሆኑት ኮ/ል ደመቀ ዘውዱ እጄን አልሰጥም ማለታቸውን ተከትሎ፣ ኮሎኔሉን ለመያዝ በመጡት የህወሃት የደህንነት አባላትና በህዝቡ መካከል ተቃውሞ ተነስቷል።

ተቃውሞው ዛሬም ቀጥሎ የዋለ ሲሆን፣ ከነዋሪዎችም ከመንግስት ታጣቂዎችም በርካታ ሰዎች ተገድለዋል። የገዢው ፓርቲ ንብረት የሆኑ በርካታ የንግድ ተቋማት ወድመዋል።

የህዝቡ የትኩረት ማእከል የሆኑት ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ ከእገታ የወጡ ሲሆን፣ ህዝቡ አጅቦ እየጨፈረ እንደወሰዳቸው ታውቛል። ኮሎኔሉ በአሁኑ ጊዜ ግን የት እንዳሉ ለማወቅ አልተቻለም። ትናንት ምሽት በነበረው የተኩስ ልውውጥ የወልቃይት ጠገዴ የአማራ ማንነት የኮሚቴ አባላት ከሆኑት መካከል 3 ሰዎች ተገድለዋል።

የተኩሱ ልውውጥና ውጥረቱ እስከምሽት የቀጠለ ሲሆን፣ በእስር ላይ የሚገኙ የኮሚቴው አባላት እንዲፈቱ ጥያቄ ቀርቧል። በተለያዩ የሰሜን ጎንደር ወረዳዎች የሚገኙ ነዋሪዎች ወደ ጎንደር በማቅናት ህዝባዊ አመጹን ተቀላቅለው ውለዋል።

በጎንደር ታሪክ በዚህ መጠን ህዝባዊ ተቃውሞ ሲካሄድ የመጀመሪያ ነው የሚሉት ነዋሪዎች፣ የወልቃይት ጠገዴ ህዝብ ጥያቄ ካልተመለሰ ግጭቱ ከዚህ በባሰ ሁኔታ ተያይዞ ይቀጥላል ሲሉ ያስጠነቅቃሉ።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሰራተኞቹ ወደ ጎንደር እንዳይጓዙ አስጠንቅቋል።