ኢሳት (ሃምሌ 5 ፥ 2008)
በቅርቡ በአዲስ አበባ ከተማ መሰራጨት በጀመረው የአጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት (ኮሌራ) በሽታ እስካሁን ድረስ በትንሹ ስድስት ሰዎች ሞቱ።
በሁሉም ክፍለ-ከተሞች በመሰራጨት ላይ ባለው በዚሁ ወረርሽን እስከ 2ሺ የሚደርሱ ነዋሪዎች በበሽታው መያዛቸውንና በሽታውን ለመቆጣጠር እየተደረገ ያለው ጥረት አልባት አለማምጣቱን በሃገር ውስጥ ያሉ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
በበሽታው የተያዙ በርካታ የከተማዋ ነዋሪዎች በተለያዩ ጊዜያት የኮሌራ በሽታ መከላከያ ጣቢያዎች ህክምና እየተደረገላቸው ሲሆን፣ በከተማዋ ተባብሶ የቀጠለው የመጠጥ ውሃ እጥረት የበሽታውን ስርጭት እያዛመተው መሆኑን የጤና ባለሙያዎች አስረድተዋል።
እስከተያዘው ሳምንት ብቻ በዚሁ የበሽታ ወረርሽኝ በትንሹ ስድስት ሰዎች መሞታቸው ቢረጋገጥም በርካታ የታመሙ ሰዎች መኖራቸው የሟቾች ቁጥር ሊጨምር ይችላል ተብሎ ተሰግቷል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የበሽታውን ስርጭት ለመቆጣጠር ወደ 1ሺ የሚጠጉ የጤና ባለሙያዎችን በከተማዋ አሰማርቶ የሚገኝ ሲሆን፣ በሁሉም ክፍለ ከተሞች የሚገኙ 26 ወረዳዎች በወረርሽኙ ጉዳት እየደረሰባቸው መሆኑ ታውቋል።
የአዲስ አበባ የጤና ቢሮ በወረርሽኙ የደረሰ ጠቅላላ ጉዳት ቢገለጽ በነዋሪው ዘንድ መረበሽን ያስከትላል በሚል መረጃውን ሙሉ ለሙሉ ከመልቀቅ መቆጠቡን አቶ ሙሉጌታ አድማሱ የተባሉ የቢሮው ተወካይ ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት ያለው የክረምት ወቅት ወረርሽኙ እየተባባሰ እንዲሄድ አስተዋጽዖ ሊያደርግ እንደሚችል ተወካዩ አክለው ለመገናኛ ብዙሃን አስረድተዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከአዲስ አበባ ውጭ በኦሮሚያና ሶማሊ ክልሎች በሚገኙ ስድስት ዞኖች በቅርቡ ተቀስቅሶ በነበረ ተመሳሳይ ወረርሽን 19 ሰዎች መሞታቸውን ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።
የአለም ጤና ድርጅት ከሌሎች አካላት ጋር በመሆን በአዲስ አበባ ከተማ እየተሰራጨ ያለውን የኮሌራ ስርጭት ለመቆጣጠር ጥረት እያደረገ መሆኑን ገልጿል።
በሽታው ከ10 እስከ 20 በሚሆኑ ሰዎች ላይ ከታየና ከተረጋገጠ የአለም ጤና ድርጅት በሽታው ወረርሽን እንደሆነ ይገልጻል።
ይሁንና የከተማዋ አስተዳደር በሽታው ስላለበት ሁኔታ በይፋ ማረጋገጫን ከመስጠት ተቆጥቧል።