በኢትዮጵያ 21ሺ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የውሃ አገልግሎት የላቸውም ተባለ

ኢሳት (ሃምሌ 5 ፥ 2008)

በኢትዮጵያ በተለያዩ ክልሎች ከሚገኙ 35ሺ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መካከል ወደ 21ሺ የሚጠጉት የውሃ አገልግሎት የሌላቸው መሆኑን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ይፋ አደረገ።

በተለይ በድርቅ በተጎዱ ክልሎች ውስጥ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች የውሃ አገልግሎት የማያገኙ በመሆኑ ትምህርታቸውን የሚያቋርጡ ተማሪዎች እየጨመረ እንደሚሄድ ምክንያት መሆኑ ታውቋል።

ድርጅቱ ከተለያዩ አለም-አቀፍ ተቋማት ጋር በመተባበር ትምህርት ቤቶቹ የውሃ አገልግሎት እንዲያገኙ ጥረትን ቢያደርጉም በገንዘብ እጥረት የተነሳ እቅዱ ውጤታማ ሊሆን አለመቻሉን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በጉዳዩ ዙሪያ ባወጣው ሪፖርት አመልክቷል።

በጥናቱ ተካተው ከነበሩት 35ሺ ትምህርት ቤቶች መካከል ወደ 22ሺ የሚሆኑት ከተማሪዎች ምቹ የሆነ የንፅህና መጠበቂያ እንደሌላቸው ከሪፖርቱ ለመረዳት ተችሏል።

በድርቅ በተጎዱ አካባቢዎች የሚገኙ በሺዎች የሚቆጠሩ ትምህርት ቤቶች የውሃ አገልግሎት የሌላቸው በመሆኑ ወደ 3 ሚሊዮን የሚጠጉ ተማሪዎች ትምህርታቸውን እንዲያቋርጡ ምክንያት መሆኑን የተባበሩት መንግስታት የህጻናት መርጃ ድርጅት ይገልጻል።

ከ35 ሺ ትምህርት ቤቶች መካክል 2ሺ 150 የሚሆኑት የተሻሻለ የመጸዳጃ ቤት የሌላቸው ሲሆን፣ በጣም አነስተኛ የሆኑት ብቻ የውሃ አገልግሎት የሚያገኙ መሆኑን ሪፖርቱ አስፍሯል።

የውሃ እጥረቱ በተማሪዎች ዘንድ የሚያስከትለውን የንጽህና ችግር ለመከላከል ሲባል ከስድስት ሺህ የሚበልጡ ትምህርት ቤቶች ውሃን በተሽከርካሪ ለማቅረብ ጥረት እየተደረገ መሆኑም ታውቋል።

ይሁንና የአቅም እና የገንዘብ እጥረት ችግሩን ለመቅረፍ በሚደረገው ጥረት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድሮ እንደሚገኝ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አክሎ አመልክቷል።

ተማሪዎች የውሃ አገልግሎት በሌለባቸው ትምህርት ቤቶች እንዲማሩ መደረጉ የተለያዩ ውሃ ወለድ ተላላፊ በሽታዎችን እንዲቀሰቀሱ ምክንያት ይሆናሉ ተብሎ የተሰጋ ሲሆን፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አለም አቀፍ ተቋማት ድጋፋቸውን እንዲያደርጉ ጠይቋል።