ኢሳት (ሃምሌ 5 ፥ 2008)
መቀመጫቸውን በኤርትራ ካደረጉ ሃይሎች ጋር ግንኙነት ኣላቸው የተባሉ ታጣቂዎች በሰሜን ጎንደርና ትግራይ ክልሎች ከመንግስት የጸጥታ ሃይሎች ጋር የተኩስ ልውውጥ በማድረግ ላይ መሆናቸውን መንግስት ማክሰኞ ምሽት ገልጸ።
ታጣቂዎች ሴቶችንና ህጻናትን ከለላ በማድረግ ከመንግስት የጸጥታ ሃይሎች ጋር ተኩስ በመክፈትና ቦንብ በመወርወር ጉዳት አድርሰዋል ሲል የብሄራዊ መረጃ ደህንነት አገልግሎትና የፌዴራል ፖሊስ የጋራ የጸረ-ሽብር ግብረሃይል አስታውቋል።
ግብረ ሃይሉ በታጣቂ ሃይሎች ድርሷል ያለው ጉዳት በዝርዝር ያልገለጸ ሲሆን፣ የጉዳቱ መጠን በቀጣይ ለህዝብ ይፋ ይደረጋል ሲል መግለጹን የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
እጅ አንሰጠም ብለው ከሚገኙት ታጣቂዎች በተጨማሪ በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን ጠገዴ ወረዳ ሶሮቃና ቁርቢ አካባቢ እንዲሁም ትግራይ ክልል ምዕራባዊ ዞን ፀገዴ ወረዳ ዳንሻና አካባቢው በኤርትራ ከመሸጉ ሃይሎች መመሪያን ተቀብለው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ታጣቂዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል ሲል ግብረ ሃይሉ አስታዉቋል።