ግብጽ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ 143 ስደተኞችን በቁጥጥር ስር አዋለች

ኢሳት (ሃምሌ 4 ፥ 2008)

የግብፅ መንግስት በህግ-ወጥ መንገድ የዉሃ ግዛት በመጠቀም ወደ አዉሮፓ ለመጓዝ ሙከራን አድርገዋል የተባሉ ኢትዮጵያንን ጨምሮ 143 ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸዉን አስታወቀ።

በ24 ሰዓታት ዉስጥ ለሁለተኛ ጊዜ በፀጥታ ሀይሎች በተወሰደዉ በዚሁ ዘመቻ 322 ስድተኞች በቁጥጥር ስር ሊውሉ መቻላቸዉን አል-አህራም የተሰኘ ጋዜጣ የግብፅ የባህር ሀይል ሃላፊዎችን ዋቢ በማድረግ ሰኞ ዘግቧል።

የሀገሪቱ የባህር ሀይል ሀላፊ የሆኑት ብርጋዴል ጄኔራል ሞሐመድ ሳሚር ኢትዬጵያንን ጨምሮ ከሱዳን ፣ ሶሪያ እና የሌሎች ሀገራት የመጡ ስደተኞች ለአሳ ማጥመጃ የሚሆኑ ጀልባዋችን በመጠቀም ወደ አዉሮፓ ለመጓዝ ጥረት ማድረጋቸዉን ገልጸዋል።

በአቡ ቀር ወደብ በቁጥጥር ሰር የዋሉት ስደተኞች ለግብፅ መርማሪ ሀይሎች ተላልፈዉ መሰጠታቸዉንና ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድባቸው አክለው አስረድተዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በግብፅ በኩል ወደ ደቡብ የአዉሮፓ ሀገራት ለመሰድድ ጥረትን የሚያድርጉ የኢትዬጵያ ፣ የኤርትራ ሱዳንና ሌሎች ሀገራት ስደተኞች በሀገሪቱ የዉሃ ግዛት ላይ መበራከታቸዉን የግብፅ ባለስልጣናት ለመገናኛ ብዙሀን ገልፀዋል።

በአሁኑ ወቅት በመቶዋች የሚቆጠሩ ስደተኞች በተለያዩ የግብፅ እስር ቤቶች እንደሚገኙ ታዉቋል።

የአለም አቀፍ ስደተኞች ድርጅት (IOM) እና ሌሎች አለም አቀፍ ተቋማት በሺዎች የሚቆጠሩ  ኢትዬጵያውያን በጎረቤት ሀገራት በኩል ወደ ተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች በመሰደድ ላይ መሆናቸዉ ስጋት መፍጠሩን በቅርቡ መግለፃቸዉ ይታወሳል።

ከአንድ ሳምንት በፊት በምዕራብ አፍሪካ በኩል ወደ ደቡብ አፍሪካ ለመግባት በእቃ መጫኛ ተሽከርካሪ ሲጓዙ ከነበሩ በርካታ ኢትዬጵያዉያን ስደተኞች መካከል 19ኙ አየር አጥሯቸዉ ህይወታቸዉ ማለፉ የሚታወቅ ነዉ።