በደቡብ ሱዳን በተቀሰቀሰው ግጭት ከ200 ሰዎች በላይ ተገደሉ

ኢሳት (ሃምሌ 4 ፥ 2008)

ከቀናት በፊት በድቡብ ሱዳን መዲና ጁባ በመንግስትና በአማፂያን ቡድን ወታደሮች መካክል የተቀሰቀሰዉ ግጭት መባባስን ተከትሎ ከ200 በላይ ሰዎች ተገደሉ።

ይኸው በመዲናይቱ ጁባ ለአራተኛ ቀን ቀጥሎ የሚገኘዉ ግጭት አዲሲቷን ሀገርን ወደ እርስ በርስ ጦርነት ይወስዳታል ተብሎ የተሰጋ ሲሆን የተለያዩ ሀገራት የኤምባሲ ሰራተኞቻቸዉን ማስወጣት ጀምረዋል።

ከወራት በፊት በደቡብ ሱዳን መንግስትና በሪክ-ማቻር የሚመራዉ አማፂ ቡድን የጋራ ብሔራዊ መንግስት ለመመስርት የደረሱትን ስምምነት ተከትሎ ወደ 1 ሺ የሚጠጉ የአማፂ ቡድን ወታደሮች ወደ መዲናይቱ ጁባ መግባታቸዉ ይታወሳል።

ለሪክ-ማቻር ጥበቃን ያደርጋሉ የተባሉ እነዚሁ ወታደሮች ካለፈዉ አርብ ጀምሮ ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ ግጭት ዉስጥ መግባታቸዉን የተለያዩ አካላት በመግለፅ ላይ መሆናቸውን BBC ዘግቧል።

በሁለቱ ወገኖች መካከል ተደርሶ የነበረዉ ሰምምንት በሚጠበቀዉ ጊዜ ውስጥ ተግባራዊ አለመሆኑ ለግጭቱ መንሰኤ ሊሆን እንደሚችል የተገለፀ ሲሆን የፐሬዝዳንት ሳልባ-ኪር እና ሪክ-ማቻር ወታደሮች በጁባ መንገዶች ተኩስ በመለዋወጥ ላይ መሆናቸዉ ታዉቋል።

ሰኞ ለአራተኛ ቀን በዘለቀዉ በዚሁ አዲስ ግጭት እስካሁን ድረስ ከ200 በላይ ሰዎች መገደላቸዉንና ቁጥራቸዉ በትክክል ያልታውቁ ነዋሪዎችም መቁሰላቸውን መገናኛ ብዙሀን ዘግበዋል። ነፃነቷን ያወጀችበትን አምስተኛ አመት ለማክበር በዝግጅት ላይ የምትገኘዉ ደቡብ ሱዳን በመካሄድ ላይ ባለዉ ግጭት አሜሪካና ህንድ አስፍላጊ ያሏቸዉን የኤምባሲ ሰራተኞችን እንዲወጡ አድርገዋል።

የቻይና መገናኛ ብዙሀን በበኩላቸዉ ሁለት የሀገሪቱ የሰላም አስካባሪ አባላት መገደላቸዉንና ሌሎች በርካታ ሰላም አስከባሪዎች ጉዳት እንደደረሰባቸዉ የዘገቡ ሲሆን ከ10 ሺ የሚበልጡ ሰዎች ከመኖሪያ ቀያቸዉ መፈናቀላቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ይፋ አድርጓል።

ጁባ የሚገኘዉ የሀገሪቱ አለም አቀፍ አዉሮፕላን ጣቢያ በዙሪያዉ ግጭቶች እየተካሄደ መሆኑን የገለፁ የአይን እማኞች በርካታ ሰዎችን አስጠልሎ የሚገኝዉ የተባበሩት መንግስታት መጠለያ ጣቢያ አቅራቢያ ከባድ ግጭት በመካሄድ ላይ መሆኑን ለመገናኛ ብዙሀን አስረድተዋል።

የአማፂ ቡድን መሪ የሆኑትና በቅርቡ የምክትል ፕሬዝዳንት ስልጣናቸዉን የተረከቡት ሪክ-ማቻር በበኩላቸዉ የፕሬዝዳንት ሳልባ-ኪር መንግስት በአማፂ ወታደሮች ላይ የአየር ጥቃትን መፈፅም እንደጀመረ ሰኞ ገልፅዋል።

አሜሪካና የተልያዩ ሀገራት በደቡብ ሱዳን የተቀሰቀሰዉን ግጭት አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን በመግለፅ ላይ ሲሆኑ ህንድ ዜጐቿን ወደ ሀገሪቱ እንዳይጓዙ አሳስባለች።

ኢትዩጵያን ጨምሮ የተለያዩ ሃገራት በርካታ ወታደሮችን በደቡብ ሱዳን በሰላም አስከባሪነት አሰማርተው እንደሚገኙ ይታወቃል።

በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በንግድና በተለያዩ ስራዎች ላይ ተሰማርተው እንደሚገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ።