ኢሳት (ሃምሌ 1 ፥ 2008)
ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚያስገባ የመግቢያ ፈተና ተሰርቋል ተብሎ በማህበራዊ ድረገጾች መሰራጨቱ የስርዓቱን ዝርክርክነትና የአመራር ጉድለት የሚያሳይ መሆኑ ተገለጸ። መንግስት በፈተና መሰረቅ ጉዳይ ላይ ምንም አለማለቱ በተማሪዎቹ ላይ ችግር መፍጠሩም ታውቋል።
ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የመግቢያ ፈተና በማህበራዊ ድረገጾች መሰራጨቱን ተከትሎ፣ የትምህር ሚኒስቴር የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና የሚሰጥበት ቀን ለሁለተኛ ጊዜ አራዝሞ ሌላ ፈተና እንደሚያዘጋጅ አስታውቆ እንደነበር ይታወሳል።
ሚኒስቴሩ የመጀመሪያ ፈተናን መሰረቅን ተከትሎ፣ ብሄራዊ ፈተናው ከሰኔ 27 እስከ ሰኔ 30 ቀን 2008 ዓም እንደሚካሄድ ይፋ አድርጎ ነበር። ይሁንና የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላላ ምክር ቤት የፈተናው ጊዜ ከረመዳን ጾም ጋር የተገናኘ ነው ብሎ ያቀረበውን ጥያቄ ተቀብሎ ፈተናው ለሁለተኛ ጊዜ እንዲራዘም ማደረጉን መግለጹ አይዘነጋም።
ለሁለተኛ ጊዜ እንዲራዘም በተደረገው የጊዜ ሰሌዳ መሰረትም የብሄራዊ መልቀቂያ ፈተናው ከሃምሌ 4 ቀን እስከ ሃምሌ 7 2008 አም ድረስ እንደሚሰጥ ተገልጾ ነበር።
ሆኖም፣ በሚቀጥለው ሳምንት ይሰጣል የተባለው የእንግሊዝኛ ፈተና በዚህ በያዝነው ሳምንት ለኢሳት ደርሶታል። ኢሳት መረጃው እንደደረሰ ለት/ሚኒስትር ምላሽን እንዲሰጥበት ጥያቄ ቢያቀርብም፣ እስካሁን ድረስ የተሰጠ ምላሽ አለመኖሩም ተመልክቷል።
ባለፉት ሁለት ቀናት ለኢሳት የደረሰው ፈተና በተለያዩ ማህበራዊ የመረጃ ምንጮች እየተበተነ እንደሚገኝና ማን እንደበተነው የሚታወቅ ነገር አለመኖሩም ተመልክቷል። ሾልኮ ወጣ የተባለው ብሄራዊ ፈተና በዕርግጥ ትክክለኛ ከሆነ ፍትሃዊነቱ አጠያያቂ ነው ሲሉ አንዳንድ ወገኖች ለኢሳት ተናግረዋል።
የኢሳት ማኔጂንግ ዳይሬክተር ጋዜጠኛ አበበ ገላው ትምህርት ሚኒስቴር ፈተናው መሰረቅ አለመሰረቁ የኢትዮጵያ መንግስት መግለጫ መስጠት ይኖርበታል ብለዋል።
ተፈታኝ ተማሪዎች ተረጋግተው ፈተና ላይ እንዲቀመጡ ትምህርት ሚኒስተር ሃላፊነቱን መወጣት አለበት ያሉት አቶ አበበ ገላው፣ ድርጊቱ የስርዓቱ የመምራት አቅም ማጣትና መዝረክረክ ቁልጭ አድርጎ ያሳየ ነው ነው ሲሉ በኢህአዴግ ውስጥ ያለውን ምስጢር ያለመጠበቅ ችግር ገልጸዋል።
ተሰርቆ ወጥቷል የተባለውና በቀጣይ ሳምንት ይሰጣል ተብሎ የሚጠበቀው ፈተና በእርግጥም ትክክለኛ ከሆነ በርካታ ተማሪዎች ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ያሳድራል ተብሎ ይጠበቃል።
የብሄራዊ ፈተናው በመሰረቁ ምክንያት ከ200 ሺ የሚበልጡ ተማሪዎች ከፈተናቸው የተስተጓጎሉ ሲሆን፣ መንግስት ከ200 ሚሊዮን ብር የሚበልጥ ኪሳራ እንደደረሰበት ለመረዳት ተችሏል።
ለፈተናው በዝግጅት ላይ የነበሩ ተማሪዎች በበኩላቸው መንግስት ፈተና የሚሰጥበትን ቀን በአግባቡ ሳያጤን የሚሰጠው ውሳኔ በጥናት ፕሮግራማቸው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩን የገለጸው ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።
ትምህርት ሚኒስቴር በበኩሉ ፈተናው በተደራጀ እና ምስጢራዊነቱን በጠበቀ መልኩ የህትመትና የስርጭት ስራው እንደሚከናወን አስታውቆ እንደነበር ይታወሳል።
በፈተና ስርቆት ላይ የተሰማሩ ግለሰቦች ላይ አስፈላጊው ማጣራት ተደርጎ እርምጃ እንደሚወስድ ገልጾ የነበረው ት/ሚኒስቴር፣ ፈተናውን በሰረቁት ሰዎች ላይ ምን አይነት እርምጃ እንደተወሰደ የገለጸው ነገር የለም።