ኢሳት (ሃምሌ 1 ፥ 2008)
የኢትዮጵያ ደቡብና ደቡባዊ የምስራቅ ግዛቶች ዳግም በከፋ የድርቅ አደጋ ሊጠቁ እንደሚችሉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አሳሰበ።
በወቅታዊ የሃገሪቱ ድርቅ ዙሪያ ሪፖርቱን ያወጣው ድርጅቱ ዳግም ሊከሰት በሚችለው የድርቅ አደጋ በርካታ የአርብቶ አደር አካባቢዎች እስከቀጣዩ የፈረንጆች አመት ድረስ ጉዳት ሊደርስባቸው እንደሚችል አስታውቋል።
በደቡባዊ የኢትዮጵያ ግዛቶች በተያዘው የክረምት ወቅት መጣል የነበረበት ዝናብ በበቂ ሁኔታ ባለመገኘቱና ሊከሰት ይችላል የተባለ የአየር ጸባይ ለውጥ አሁንም ድረስ ስጋት መሆኑን ድርጅቱ ገልጿል።
ዳግም ሊከሰት የሚችለው ይኸው የድርቅ አደጋ በአሁኑ ወቅት ያለውን 10.2 ሚሊዮን የአስቸኳይ ጊዜ የምግብ ተረጅዎች ቁጥር ከፍ እንደሚያደርገውም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በወቅታዊ ሪፖርቱ አመልክቷል። አርብቶ አደሮች ከእንስሳት ተዋፅዖ የሚያገኟቸው የምግብ አይነቶች በመጠን እየቀነሰ ሊሄድ እንደሚችል ያስታወቀው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ ቅድመ-ጥንቃቄ ካልተደረገ ድርቁ የሚያደርሰው ጉዳት ከሚገመተው በላይ ሊሆን እንደሚችል አክሎ አሳስቧል።
በስድስት ክልሎች ተከስቶ የሚገኘው የድርቅ አደጋ እያደረሰ ያለው ጉዳት በሃገሪቱ ታሪክ በ50 አመት ውስጥ ሲከሰት የከፋው እንደሆነ የተለያዩ አካላት በመግለጽ ላይ ናቸው።
ለምግብ ድጋፍ ለተጋለጡ ሰዎች መድረስ ያለበት የእርዳታ አቅርቦት በጎረቤት ጅቡቲ ወደብ ቢደርስም በወደቡ የተከሰተው የእቃዎች መጨናነቅ ተፅዕኖ ማሳደሩ ታውቋል።
ይኸው በወደቡ ለሁለተኛ ጊዜ የተከሰተው መጨናነቅ የእርዳታ እህሉ ለተረጂዎች እንዳይደርስ ያደረገ ሲሆን፣ በተለይ በአማራና ትግራይ ክልሎች ያሉ ከሶስት ሚሊዮን በላይ ተረጂዎች ለችግር መዳረጋቸውን የተባበሩት መንግሳታት ድርጅት ይፋ አድርጓል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የብሪታኒያው የህጻናት አድን ድርጅት በኢትዮጵያ ተከስቶ ያለው የድርቅ አደጋ እጅግ አሳሳቢ ወደ ሆነ ምዕራፍ መሸጋገሩን አርብ አስታውቋል።
ወደ ስድስት ሚልልዮን የሚጠጉ ህጻናት ለአስቸኳይ የምግብ እርዳታ ተጋልጠው እንደሚገኙ የገለጸው ድርጅቱ የአለም አቀፍ ማህበረሰብ ድጋፍ ለችግሩ ከመቼውም ጊዜ በላይ ወሳኝ ሆኖ መገኘቱን ባወጣው መግለጫ አመልክቷል።
በኢትዮጵያ የድርጅቱ ተወካይ የሆኑት ጆን ግራም ቀጣዮቹ ሶስት ወራቶች በመባባስ ላይ ያለውን ችግር ለመቅረፍ እጅግ ወሳኝ ወቅት ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የአለም አቀፉ ማህበረሰብ ለተረጂዎች የሚያስፈልገውን የምግብ ድጋፍ በቀጣዮቹ ሶስት ወራቶች ውስጥ ማድረስ ካልቻለ እስካሁን ድረስ ድርቁን ለመመከት የተደረጉ ጥረቶች ዋጋ ሊያጡ እንደሚችሉ ሃላፊው አስረድተዋል።
ድርቁ በተለይ በህጻናት ላይ እያደረሰ ያለው ጉዳት እየተባባሰ መምጣቱን ያስታወቁት የህጻናት አድን ድርጅቱ ተወካይ በተያዘው የፈረንጆች 2016 ዓም የመጀመሪያዎቹ ሶስት ወራቶች ብቻ 108ሺ ህጻናት ለከፋ የምግብ እጥረት መዳረጋቸውን አክለው ገልጸዋል።
ሃገሪቱ ለሁለት አመት ለዘለቀው የድርቅ ጉዳት ለማገገም በትንሹ ከሁለት እስከ ሶስት አመት ድረስ ሊፈጅባት እንደሚችል የብሪታኒያው የህጻናት አድን ድርጅት በሪፖርቱ ላይ አስፍሯል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የተለያዩ አለም-አቀፍ የእርዳታ ድርጅቶች በኢትዮጵያ ተከስቶ ያለው የድርቅ አደጋ ወደ ረሃብ ሊሸጋገር ይችላል ሲሉ ስጋታቸውን ሲገልጹ መቆየታቸው ይታወሳል።
መንግስት በበኩሉ ለጋሽ ተቋማት የሚሰጡትን ስጋት በማስተባበል ድርቁ የከፋ ችግርን እንዳያደርስ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን በመግለጽ ላይ ናቸው።