ኢሳት (ሰኔ 30 ፥ 2008)
በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በረሃብ እየተሰቃዩ ባሉበት በአሁኑ ወቅት፣ የአለም አቀፍ ማህበረሰብ በሌሎች ትናንሽ ጉዳዮች ላይ ማተኮሩ አግባብ አይደለም ሲሉ አንድ የተባበሩት መንግስታት መልዕከተኛ ወቀሳ አቀረቡ።
የቀድሞ የአየርላንድ ፕሬዚደንት ሜሪ ሮቢንሰን ይህንን የተናገሩት ኢትዮጵያ ውስጥ ስለተከሰተው ድርቁ ማብራሪያ ከተሰጣቸው በኋላ መሆኑ ታውቋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት መልዕከተኛ ሚስ ሜሪ ሮቢንሰን ለመገናኛ ብዙሃን አንደተናገሩት፣ በአሁኑ ሰዓት የአለም አቀፍ ማህበረሰብ እየተነጋገረ ያለው በትናንሽ ጉዳዮች ላይ በመሆኑ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ስለተከሰተው ረሃብ ትኩረት አለመሰጠቱን ኮንነዋል። መገናኛ ብዙሃንን ጨምሮ የአለም አቀፍ ማህበረሰብ ስለ እንግሊዝ ህዝበ-ውሳኔ፣ ወደ አውሮፓ ስለሚገቡ ስደተኞች መጨመርና እና በአለም ዙሪያ በሚከሰቱ ግጭቶች ላይ ትኩረት በማድረጋቸው ኢትዮጵያ ውስጥ እየተከሰተ ስላለው ሰብዓዊ ቀውስ በቂ ትኩረት አልሰጡም ሲሉ ክስ አቅርበዋል።
ባለፉት ሰላሳ ዓመታት ውስጥ ተከስቶ የማያውቅ ርሃብ በኢትዮጵያ ውስጥ መከሰቱንና ከ10 ሚሊዮን በላይ ዜጎች በርሃብ መጠቃታቸውን አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን መዘገባቸው ይታወሳል።
በድርቁ የተጠቁት አብዛኞቹ ህጻናትና ሴቶች መሆናቸውን አለም አቀፍ ረድዔድ ድርጅቶች ገልጸዋል። በኢትዮጵያ ውስጥ በተከሰተው ድርቅ ከሶስት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ህጻናት ከትምህርት ገበታቸው እንደቀሩ ዩኒሴፍ በቅርቡ መግለጹ ይታወሳል።
በተመሳሳይ መልኩም በኢትዮጵያ የተከሰተውን ድርቅ ተከትሎ በሴቶች ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ ጉዳዮች ድርጅት (UNOCHA) በቅርቡ ማስታወቁ አይዘነጋም።
ድርቁ ነፍሰጡሮችንና የሚያጠቡ እናቶችንና በከፍተኛ ሁኔታ እየጎዳቸው እንደሆነ የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ ጉዳዮች ድርጅት ባለፈው ሳምንት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። በድርቁ መባባስ የተነሳ ነፍሰጡሮችና የሚያጠቡ እናቶች ከምግብ አቅርቦት ማነስ ጋር የተያያዙ ውስብስብ የጤና ችግሮች እየደረሱባቸው እንደሆነ በወቅታዊ የሃገሪቱ የድርቅ አደጋ ዙሪያ ሪፖርትን ያወጣው ተመድን ዋቢ አድርግን መዘገባችን ይታወሳል።