ኢሳት (ሰኔ 30 ፥ 2008)
ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ ያጋራ ንቅናቄ ሊቀመንበር አቶ ኦባንግ ሜቶ በአዲስ አበባ እየፈረሱ ባሉ ቤቶች ስለተፈናቀሉ ከ20ሺ በላይ ዜጎች እና በአንድነት ፓርቲ አመራር ሃብታሙ አያሌው ላይ የሚፈጸመውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት አስመልክተው ለዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ግልጽ ደብዳቤ ጻፉ።
በሰኔ ወር ውስጥ በላፍቶ ክፍለ ከተማ ቀርሳ፣ ኮንቶማ ማንጎ ወረገኑ እና ሃናማሪያም ተብለው ከሚጠሩ መንደሮች ከህጻናት ጀምሮ እድሚያቸው 93 ዓመት የሚደርሱ አዛውንቶች ድረስ ቤታቸው ፈርሶ ንብረታቸው ተበትኖ መፈናቀላቸው ሃገሪቱን ከቀውስ ወደ ሌላ የከፋ ቀውስ ይመራታል ሲሉ አቶ ኦባንክ አስጠንቅቀዋል።
የአንድነት አመራር አቶ ሃብታሙ አያሌው በከፍተኛ ህመም እየተሰቃየ ለህክምና ወደ ውጭ ሃገር እንዳይወጣ መከልከሉን የኮነኑት አቶ ኦባንግ፣ የሃብታሙ ህይወት በዚህ መልኩ ቢያልፍ የህወሃት ኢህአዴግ ባለልስጣናት ተጠያቂ ይሆናሉ ብለዋል።
አቶ ኦባንግ ይህን ደብዳቤ ለምን ለውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ መጻፍ እንደመረጡ ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ ተናግረዋል።
“የሃገሪቱ አመራርነት ስልጣን በህወሃት ቁጥጥር ስር በመሆኑ፣ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ሃይለማሪያም ይልቅ ዶ/ር ቴዎድሮስን መርጫለሁ” ብለዋል።
አቶ ኦባንግ የህወሃት አመራሮች እና አባላት ራሳቸውን ጥቃት በሚደርስባቸው የተፈናቀሉ ዜጎችና የአልጋ ቁራኛ በሆነው ሃብታሙ አያሌው ቦታ አድርገው እንደተመለከቱ በማሳሰብ፣ ዘላለም የሚገዛ መንግስት የለም በማለት የገዢው ስርዓት ሰዎች መጪውን ጊዜ እንዲያስቡ መክረዋል።