ኢሳት (ሰኔ 30 ፥ 2008)
የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በፅኑ ህመም ላይ የሚገኙት አቶ ሃብታሙ አያሌው ከሃገር ውጭ እንዲታከሙ የቀረበለትን ጥያቄ የተሟላ አይደለም ሲል ሃሙስ ምላሽ ሰጠ።
ከቀናት በፊት በጉዳዩ ላይ ውሳኔን ይሰጣል ተብሎ የነበረው ፍርድ ቤት የቀረበለት ማስረጃ በቦርድ የተደገፈ አይደለም ሲል ማስረጃውን አስተካክሎ እንዲቀርብለት ምላሽን መስጠቱን ጉዳዩን እየተከታተሉ የሚገኙት የአቶ ሃብታሙ ቤተሰቦች ለኢሳት አስታውቀዋል።
ከሁለት ሳምንት በፊት ጀምሮ በጽኑ ህመም ላይ የሚገኘውና የአንድነት ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ የሆነው አቶ ሃብታሙ አያሌው አሁንም ድረስ የጤና ሁኔታ አሳሳቢ ሆኖ መቀጠሉ ታውቋል።
አምነስቲ ኢንተርናሽናል የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት መንግስት በአቶ ሃብታሙ አያሌው ላይ ከሃገር እንዳይወጣ ጥሎ የሚገኘውን እገዳ እንዲያነሳ ዘመቻን እያካሄዱ ይገኛል።
አቶ ሃብታሙ አያሌው በአሁኑ ወቅት የህመም ማስታገሻን ብቻ እያገኘ እንደሆነ የሚናገሩት ቤተሰቦች ፍርድ ቤት እንዲሟላ ሲል የሰጣቸውን ምላሽ ለማሳካት የተቻላቸውን ጥረት እያደረጉ እንደሆነ ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ አስረድተዋል።
አምነስቲ ኢንተርናሽናል አቶ ሃብታሙ አያሌው በእስር ቤት በነበረው ቆይታ የተፈጸመበት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችና ስቃይ ላጋጠመው ጽኑ ህመም ምክንያት መሆኑን ሰሞኑን መግለጹ ይታወሳል።
የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱ ለኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝ በጻፈው ደብዳቤ አቶ ሃብታሙ ከተጣለበት እገዳ ከሰብዓዊ መብት አንጻር በአስቸኳይ ሊነሳ እንደሚገባ ጠይቋል።
አቶ ሃብታሙ አያሌው ከሌሎች የፓርት አመራር ጋር በውጭ ሃገር ካሉ ሃይሎች ጋር በማበር ህገመንግስቱን በሃይል ለማፍረስ ተንቀሳቅሷል ተብሎ በሽብርተኛ ወንጀል ተከሶ መቆየቱ የሚታወስ ነው።