ባለፈው ሳምንት በአዲስ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ቀጣና 01 መንደር 06 በተለምዶ አጠራር ቀርሳና ኮንቶማ በሚባለው አካባቢ የሚገኙ ሁለት ቤተክርስቲያኖችን ለማፍረስ የሚደረገውን እንቅስቃሴ ህዝቡ እየተቃወመ ነው።
ባለፈው ሳምንት ኡራኤል ቤተክርስቲያንን ለማፍረስ ሙከራ ሲደረግ ህዝቡ ባስነሳው ተቃውሞ ቤተክርስቲያኑ እስካሁን ሳይፈርስ ቆይቷል። ከሶስት ቀናት በሁዋላ ደግሞ የቤተክርስቲያኑ ቄስ በፌደራል ፖሊስ ተገድለዋል። አፍራሽ ግብረሃይሎች የጸበል ቦታውን ካፈረሱ በሁዋላ ፣ ሙሉውን ቤተከርስቲያን ለማፍረስ ህዝቡ ጽላት እንዲያወጣ ጠይቀዋል። ይሁን እንጅ ጽላቱን የሚያወጡ ቄሶችን ገድላችሁዋቸዋል በማለት ህዝቡ መልስ የሰጠ ሲሆን፣ ቤተክርስቲያኑም እስካሁን ከመፍረስ ድኗል። በተመሳሳይ ሁኔታም ኪዳነምረት ቤተክርስቲያንን ለማፍረስ ዛሬ እንቅስቃሴ ተጀምሯል። ካህናቱ ግን ጽላት አናነሳም እያሉ ናቸው።
ህዝቡም ተቃውሞውን በመግልጽ ላይ ነው። አንድ ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ እናት ድርጊቱ የእግዚአብሄር ቁጣ ነው ይላሉ።
መስተዳድሩ በወሰደው ጭካኔ የተሞላበት እርምጃ ከ30 ሺ በላይ ዜጎች ያለመጠለያ ቀርተዋል። ከ300 በላይ ወጣቶችም ተይዘው ታስረዋል። የወረዳውን አስተዳዳሪ አቶ ታሪክ ፍቅሬን ጨምሮ ሁለት ፖሊሶችም ተገድለዋል።