ኢሳት (ሰኔ 27 ፥ 2008)
የጣሊያን ፖሊስ በህገወጥ ሰው አዘዋዋሪነት የተጠረጠሩ 12 ኢትዮጵያውየንና 25 ኤርትራውያንን በፖሊስ ቁጥጥር ስር ማዋሉን ሮይተርስ ሰኞ ባወጣው ዘገባ አስታወቀ። ተጠርጣሪዎቹ በሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞችን ከአፍሪካ ወደ አውሮፓ በሚያዘዋውር ድርጅት ውስጥ ሲሰሩ የነበሩ ናቸው ተብሏል።
ህገወጥ አዘዋዋሪዎቹ የተከሰሱት ክስ ስደተኞችን በማስገባት፣ ዕፅ በማዘዋወር፣ እና ህገወጥ የገንዘብ ዝውውር በማካሄድ እንደሆነ ተገልጿል፣ መረጃውም በ2014 ዓም በዚያው በጣሊያን አገር የታሰረው ኤርትራዊ በሰጠው መረጃ ላይ ተመርኩዞ የተወሰደ እርምጃ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል። እስረኛው የሰጠው መረጃ በሰሜን አፍሪካና በጣሊያን ሰዎችን በማዘዋወር የታወቀውን ህገወጥ አዘዋዋሪ ቡድን ምንነትና ድርጊት ለመጀመሪያ ጊዜ በደምብ የሚገልጽ ነው ሲል ሮይተርስ የሲሲሊን ፖሊስ ጠቅሶ ዘግቧል።
ፖሊስ ከእስረኛው የተወሰደው መረጃ ተመርኩዞ በሮም በሚገኝ በአንድ የሽቶ ሱቅ ላይ በወሰደው የፍተሻ እርምጃ፣ 526,000 ዩሮ እና 25,000 ዶላር መገኘቱ ገልጿል። ከዚህ በተጨማሪም ህገወጥ ሰው አዘዋዋሪ የሰንሰለት አባላት አድራሻ የያዘ መረጃ እንደተገኘም ለማወቅ ተችሏል።
ከአፍሪካ ወደ አውሮፓ የሚሰደዱ ስደተኞች አብዛኞቹ ከሊቢያ ወደጣሊያን ሜዲትራኒያን ባህር በማቋረጥ የሚጓዙ ሲሆን፣ በዚህ አመት 60 ሺ የሚሆኑ ስደተኞች ወደጣሊያን እንደደረሱ ለማወቅ ተችሏል።
ባለፈው ግንቦት ወር በሊቢያ አድርገው ወደ አውሮፓ በጀልባ ሲጓዙ ከነበሩት ስደተኞች መካከል በሜዲትራንያን ባህር በሶስት ጀልባዎች ላይ የመስመጥ አደጋ በመደረሱ ከ 700 በላይ የሚሆኑት ስደተኞች ሰጥመው መሞታቸውን መዘገባችን ይታወሳል። በተመሳሳይ መልኩ ባለፈው ዓመት ሚያዚያ ወር በሁለት ጀልባ ላይ ተሳፍረው ከሊቢያ ወደ ጣሊያን ሲሄዱ ከነበሩት አፍሪካውያን ስደተኞች መካከል 1ሺ 300 የሚሆኑት ሰጥመው መሞታቸው አይዘነጋም።
የአውሮፓ ህብረት በበኩሉ ወደ አውሮፓ የሚጎርፉትን ስደተኞችን ለማስቆም ለአምባገነን የአፍሪካ መሪዎች የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ መምከሩ ይታወሳል።