በታንዛኒያ የሞቱ የ19 ኢትዮጵያውያን ሬሳ ኢትዮጵያ ገባ

ኢሳት (ሰኔ 20 ፥ 2008)

ለውዝ፣ ጥራጥሬና አሳ በጫነ የጭነት መኪና ተጭቀው ከታንዛኒያ ወደ ዛምቢያ ለመሻገር ከሞከሩ 95 ኢትዮጵያውያን 19ኙ ህይወታቸው ማለፉ ሲታወስ፣ የ19ኙም አስከሬን ኢትዮጵያ መግባቱ ታውቋል።

መድረሻቸውን ደቡብ አፍሪካ ለማድረግ ከኢትዮጵያ ተነስተው ኬንያ አቋርጠው ታንዛኒያ የደረሱት ኢትዮጵያውያን ዛምቢያ ላይ ህይወታቸው ያለፈው በሳምንቱ መጨረሻ ነበር።

በረሃ አቋርጠው ሲጓዙ ታፍነው ከሞቱን 19 ኢትዮጵያውያን በተጨማሪ፣ ሌሎች 76 ኢትዮጵያውየን በመኪና ውስጥ የነበሩ ቢሆንም፣ በህይወት መትረፋቸው ታውቋል።

ከ76ቱ ኢትዮጵያውያን ውስጥ 18 ዓመት ያልሞላቸው ታዳጊዎች እንደሚገኙበትም መረዳት ተችሏል።

ኢትዮጵያውየን የማስረግና የማሸጋገር ስራ ሰርተዋል የተባሉ ሶስት የዛምቢያ ዜጎች አደጋውን ተከትሎ በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተዘግቧል።

በተመሳሳይ ታንዛኒያን ለመሻገር የሞከሩ 21 ኢትዮጵያውያን ቀደም ሲል መታሰራቸው የተዘገበ ሲሆን፣ ሌሎች 21 ኢትዮጵያውያን ደግሞ በህገወጥ መንገድ ገብታችኋል ተብለው እስከ 15 ዓመት እስራት ተፈርዶባቸዋል።

ታዳጊዎችን ጨምሮ 40 ኢትዮጵያውያን በዛምቢያ ፍ/ቤት የተላለፈው ፍርድ ያሳሰባቸው ዓለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት (IOM) የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በቀረቡት ተማፅኖ ስደተኞቹ በፕሬዚደንቱ ምህረት ከእስር ቤት ተለቀዋል።