ከ100 በላይ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች መዘጋታቸው ተነገረ

ኢሳት (ሰኔ 20 ፥ 2008)

የኢትዮጵያ ህግ ከሚፈቅደው ውጪ ሲንቀሳቀሱ ተገኝተዋል የተባሉ ከ100 በላይ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ተዘጉ።

ከበርካታ አመታት በተለያዩ ማህበራዊ አገልግሎቶችን በመስጠት ስራ ላይ የነበሩ ድርጅቶች ከተቋቋሙበት አላማ ውጭ ሲንቀሳቀሱ እና ያለመንግስት ፈቃድ የባንክ ሂሳብ ሊከፍቱ የነበሩ ናቸው ሲል የኢትዮጵያ በጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ኤጀንሲ ሰኞ አስታውቋል።

የዘንድሮ በጀት አመት ሪፖርቱን ያቀረበው ኤጀንሲው እርምጃ የተወሰደባቸው 108 ድርጅቶቹ የገቢ ምንጫቸውን ጭምር ለመንግስት ሳያቀርቡ መቆየታቸውን ለሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ገልጸዋል።

አጨቃጫቂው የማህበራት አዋጅ ከጸደቀ በኋላ በየአመቱ ከስራ ውጭ የሚሆኑ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ቁጥር እየጨመረ በመሄድ ላይ ሲሆን፣ በተያዘው በጀት አመት እንዲታገዱ ከተደረጉት ድርጅቶች መካክል 14ቱ የውጭ ድርጅቶች መሆናቸው ታውቋል።

በ2008 በጀት አመት እንዲዘጉ ከተደረጉ 108ቱ ተቋማት በተጨማሪ 167 ድርጅቶች ደግሞ እስከ መጨረሻ የሚደርስ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸው የኤጀንሲው የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ሃላፊ አቶ አሰፋ ተስፋዬ ለመንግስት መገናኛ ብዙሃን ተናግረዋል።

እንዲዘጉ ከተደረጉት ድርጅቶች የተገኘ ከ19 ሚሊዮን ብር በላይ በመንግስት ገቢ እንዲሆን መደረጉን ሃላፊው አክለው ገልጸዋል።

ከጥቂት አመታት በፊት የጸደቀውን አዲሱን የበጎ አድራጎት ማህበራት አዋጅ ተከትሎ መንግስት መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ላይ ከፍተኛ ክትትልና ቁጥጥርን እያደረገ የሚገኝ ሲሆን፣ ወደ 4ሺ ይጠጋ የነበረው የድርጅቶቹ ቁጥር ከሶስት ሺ በታች መድረሱ ታውቋል።

የአዲሱ አዋጅ መጽደቅን ተከትሎ ድርጅቶቹ በዲሞክራሲና በምርጫ ትምህርቶች ላይ ተሳትፎ እንዳያደርጉ እገዳ ተጥሎባቸው ይገኛል።