በሶማሊያ ለሚገኙ ሰላም አስከባሪ ወታደሮች በየወሩ 1ሺ28 ዶላር ቢከፈላቸውም፣ ለአስተዳደራዊ ስራ 200 ዶላር ይቀነስባቸዋል ተባለ

ዜና (ሰኔ 20 ፥ 2008)

የአውሮፓ ህብረት በሶማሊያ ተሰማርተው ለሚገኙ የኢትዮጵያና የሌሎች የአፍሪካ ሃገራት ሰላም አስከባሪ ወታደሮች በየወሩ ከ20ሺ ብር የሚበልጥ የኪስ ገንዘብ እንደሚከፍል አስታወቀ።

ህብረቱ ለወታደሮቹ የሚሰጠው ይኸው ወርሃዊ ገንዘብ ወታድሮቹ ከመንግስታቸው ከሚከፈላቸው ገንዘብ የሚበልጥ መሆኑንና በመንግስታቸው በኩል ወታደሮቹ ኪስ የሚገባ እንደሆነ ቢቢሲ የህብረቱን መረጃ ዋቢ በማድረግ ሰኞ ዘግቧል።

የአውሮፓ ህብረት እያንዳንዱ ወታደር በወር 1ሺ 28 ዶላር (ከ20ሺ ብር በላይ) እየከፈለ ቢሆንም የየሃገሪቱ መንግስታት ክእያንዳንዱ ወታደር ለአስተዳደራዊ ስራ 200 ዶላርን እንደሚቀንሱም ታውቋል።

ይሁንና የአውሮፓ ህብረት በቅርቡ ለሰላም አስከባሪ ሃይሉ የሚሰጠው ድጋፍ በ20 በመቶ እንዲቀንስ መደረጉን ተከትሎ ወታደሮቹ ጥቅማጥቅማቸው በወቅቱ እንዳልተሰጣቸው ቢቢሲ በዘገባው አመልክቷል።

የአፍሪካ ህብረት የሰላም አስከባሪ ልዑክ በበኩሉ ህብረቱ ለወታደሮቹ ሲሰጥ የቆየው ጥቅማጥቅም መዘግየት በወታድሮቹ ስነልቦና ላይ ተፅዕኖን ሊያሳድር ይችላል ሲል ስጋቱን ገልጿል።

ዩጋንዳ ወታደሮቿን ከሶማሊያ ለማስወጣት መወሰኗ በተቀሩ ሰላም አስከባሪ ሃይሎች ላይ ጫናን እንደሚፈጥርና በአልሸባብ ታጣቂ ሃይል ሃይሎ ላይ የሚካሄደው ወታደራዊ እርምጃ ውጤት አልባ ሊሆን እንደሚችል ወታደራዊ ባለሙያዎች አስረድተዋል።

የአውሮፓ ህብረት በወሰደው የበጀት ቅነሳ ቅሬታ ያደረባት ዩንጋንዳ በሶማሊያ አሰማርታ የሚገኘውን ወደ 6ሺ ስላም አስከባሪ ሃይል በቅርቡ እንደምታስወጣ ይፋ ማድረጓ ይታወሳል።

በበጀት ዙሪያ የተነሳውን ይህንኑ አለመግባባት ተከትሎ የአውሮፓ ህብረት ለወታደሮቹ የዘገየውን የጥቅማጥቅም ክፍያ በቅርቡ በውዝፍ መልክ ለመክፈል በዝግጅት ላይ መሆኑን አስታውቋል።

የዩጋንዳ መከላከያ ሰራዊት ሃላፊ የሆኑት ጀኔራል ካቱምባ ዋማሊ ሃገራቸው በሶማሊያ መንግስትና ከአሜሪካ፣ ብሪታኒያ እና ቱርክን በተውጣጡ ወታደራዊ አማካሪዎች ተስፋ መቁረጥ እንዳደረባት ለቢቢሲ አስረድተዋል።

ይሁና ወታደራዊ ሃላፊው ከሃገሪቱ ደርሰዋል ስላሏቸው ድርጊቶች ዝርዝር መረጃን ከመስጠት የተቆጠቡ ሲሆን ሃገራቸው ከስድስት ሺ የሚበልጡትን ወታደሮች በቀጣዩ አመት ማስወጣት እንደምትጀምር ገልጸዋል።