ሰኔ ፳ ( ሃያ ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በመላ አገሪቱ አዳዲስ ወጣቶችን ለመመልመል የሚደረገው ጥረት ከፍተኛ እክል ያጋጠመው መሆኑን ተከትሎ፣ የኢህአዴግ ካድሬዎች አዲስ የምልመላ ስልት ይዘው ብቅ ያሉ ሲሆን፣ በተለይ በአማራ ክልል ድርቅ ባጠቃቸው አካባቢዎች የሚገኙ ወጣቶች ለውትድርና እንዲመዘገቡ ለማድረግ ከፍተኛ ስራ እየተሰራ ነው።
የክልሉ ዘጋቢያችን እንደገለጸው የብአዴን አባላት በሙሉ ሰሞኑን በወጣው የመከላከያ ሰራዊት ምልመላ ዙሪያ ወጣቱን እንዲቀሰቅሱ ከበላይ በመጣ ትእዛዝ መሰረት መመሪያ ሲሰጣቸው ነበር። በተለይ ድርቁ በስፋት በሚታይባቸው የምስራቅ አማራ ወረዳዎች ወጣቱን ከረሃብ ውትድርና ይሻላል በሚል መሪ መፈክር ፣ ለወታደሩ ከፍተኛ ደሞዝ፣ ልዩ ልዩ የሙያ ስልጠና እንደሚሰጥና ከተማው ውስጥ መኖር የሚያስችል እድል እንዳለ በመንገር እንዲያስመዘግቡ አባላቱ ጥብቅ ትእዛዝ ተሰጥቷቸዋል።
አርብ ከሰአት በሁዋላ መስሪያ ቤቶችን በመዝጋት በተደረጉ ተመሳሳይ ስብሰባዎች ላይ የተሳተፉት አንዳንድ የድርጅቱ አባላት በድርጅታቸው በኩል የቀረበውን ሰራዊት የመመልመያ ስልት አልተቀበሉትም።
በቅርቡ በምግብ ለስራ የታቀፉ ወጣቶችን በማስወጣት ፣ የምግብ እርዳታው እድሜያቸው ለገፉ እናቶችና አባቶች ብቻ ሊሰጥ መታቀዱ ፣ የሚቸገሩ ወጣቶችን ለውትድርና ለመመልመል በመታቀዱ መሆኑን የእርዳታ እህል በማከፋፈል እገዛ ከሚያደርገው የአማራ መልሶ ማቋቋም ድርጅት የመስክ ስራተኞች የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
በወልድያ የቀን ሰራተኞች በሚሰበሰቡበት ቦታ ላይ ፖሊሶች ወረቅት ይዘው በመሄድ ለተሰበሰቡ የቀን ሰራተኞች ከ8ኛ ክፍል በላይ መከላከያ ኢንጂነሪግ መግባት የሚፍልግ ወጣት በእድሉ መጠቀም ይችላል እያሉ ሰሞኑን ሲቀሰቅሱ ሰንብተዋል። አብዛኛው የቀን ሰራተኞች አልተመዘገቡም።
ሁኔታው ያሳሰባቸው ፖሊሶች፣ ሚሊሺያዎችና የቀበሌ ጸጥታ ሰራተኞች ቤት ለቤት እየሄዱ ወጣቶች ወደ መካለከያ ኢንጂነሪግ ቡገቡ የተሻለ ህይወት እንደሚመሩ በመቀስቀስ ለውትድርና እንዲመዘገቡ ለማግባባት ሲጥሩ መታየቱን የከተማው ወኪላችን ገልጿል። አንዳንድ ኑሮው የመረራቸው ወጣቶች ኢንጂነሪንግ ከሆነ እንመዘገባለን ሲሉ ወላጆቻቸውና የኢህአዴግ ተቃዋሚ ወጣቶች ደግሞ ለጦርነት ማገዶ ሊያደርጉዋችሁ ነው በማለት እንዳይመዘገቡ ለማድረግ እየሞከሩ መሆኑን ወኪላችን ገልጿል።
በቅርቡ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ግጭት ከተነሳ በሁዋላ ሰራዊት ለመመልመል የሚደረገው እንቅስቃሴ ከመቼውም ጊዜ በላይ ጨምሯል።