ኢሳት (ሰኔ 17 ፥ 2008)
በሶማሌ ክልል ከሁለት አመት በፊት የተፈጸመ የሰብዓዊ ጥሰት ወንጀልን የሚተነትነው አጭር ዘጋቢ ፊልም ተቀማጭነቱ በእንግሊዝ አገር በሆነ አንድ ግብረ ሰናይ ድርጅት ተዘጋጅቶ ለህዝብ ይፋ ሆነ።
እኤአ በ2013 እና በ2014 በኬንያ የሚገኘው ደዳብ የተባለውን የስደተኞች ካምፕ የጎበኙት The Create Trust በተባለ በሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ላይ የሚሰራው ድርጅት ሰራተኞች፣ በኢትዮጵያ መንግስት የሚፈጸመውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት በመሸሽ ወደኬንያ የሄዱትን የኦጋዴን ሴቶች አነጋግረዋል።
“ኦጋዴን፥ የኢትዮጵያ የተደበቀ ሃፍረት” በሚል የተጠናከረው ይህ አጭር ዘጋቢ ፊልም ፣ አናብ፣ ማርያማ፣ እና ፋጡማ የተባሉ ሶስት ወጣት ሴቶች በኦጋዴን ክልል በኢትዮጵያ ወታደሮች የደረሰባቸውን አስገድዶ መደፈርና ሰቆቃ ይዘረዝራል።
ዘጋቢ ፍልሙ የመገናኛ ብዙሃንና የሰብዓዊ እርዳታ ድርጅቶች በጊዜው ወደአካባቢው እንዳይገቡ ተከልክለው እንደነበር ይገልጻል። ይህ የሆነበት ምክንያት በኢትዮጵያ መንግስት ወታደሮች የተሰራው ወንጀል ተደብቆ እንዲቀር በማሰብ ነው ይላል።
በየመንና ኬንያ በእግራቸው በመጓዝ የደረሱ ሰለባዎች ዋቢ በማድረግ የተዘጋጀው ይኸው ዘጋቢ ፊልም፣ የኦጋዴን ነዋሪዎች አሰቃቂ የእስር ጊዜ እንዳሳለፉ፣ የጅምላ ግድያና እንደተፈጸመባቸውና፣ ከፍተኛ ሰቆቃ እንደደረሰባቸው ይዘረዝራል። የስደተኛ ካምፑን የጎበኙት የለቀቁት መረጃ በአካባቢው ይኖሩ የነበሩ ሴቶች በሙሉ ተደጋጋሚ አስገድዶ መድፈር ወንጀል እንደተፈጸመባቸው ያትታል።
ድብደባ፣ አስገድዶ መደፈርና ሰቆቃ ተፈጽሞብኛል ያለችው መርያማ፣ ከሁለት ዓመት ተኩል በላይ በኦጋዴን እስር ቤት ማሳለፏን ተናገራለች።
“እስኪደክመኝ ድረስ እሬሳ እንድሸከም እገደዳለሁ፣ ከዚያም በፕላስቲክ ሙሉ ሚጥሚጣ አናቴ ላይ በማድረግ እራሴን እስክስት እራሴ ላይ እንደሻሽ ያስራሉ። ከዚያም ወንዶች በጅምላ ይደፍሩኛል” ስትል ገልጻለች።
ፋጡማ የተባለችው ወጣት በበኩሏ የኢትዮጵያ ወታደሮች፣ እናንተ ኦጋዴኖች ናችሁ፣ ሙሉ በሙሉ እናጠፋችኋላን እንዳሏት ገልጻለች።
የኢህአዴግ ወታድሮች አስገድዶ መድፈርን እንደመሳሪያነት እንደሚጠቀሙና በወታደራዊ ሰፈር ሴቶችን በማስቀመጥ የወሲብ ባሪያ እንዳደረጓቸው በዚሁ ዘጋቢ ፊልም ላይ ተመልክቷል።
“በተደጋጋሚ ስለተደፈርን፣ ተለመደ፥ እኛም ተቀበልነው” ስትል የጥቃቱ ሰለባ ለዘጋቢ ፊልም አስረድታለች።
“ይህም የፊስቱላና የአነስውርነት ችግርን ጨምሮ በብዙዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት አስከትሏል። በደረሰብኝ ሰቆቃ የፊስቱላ እና የጡንቻ መሸማቀቅ ደርሶብኛል” ስትል ተናግራለች።
ሪፖርቱ ኢህአዴግ ኢትዮጵያን ማስተዳደር ከጀመረበት ከ1981 ዓም ጊዜ ጀምሮ በደቡብ ምስራቅ የአገሪቷ ክፍል የሚገኘውን ሶማሌ ጎሳ ራስን በራስ ለማስተዳደር በመጠየቁ የዘር ማጥፋት ዘመቻ የሚመስል የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሰለባ ሆኖ ቆይቷል ይላል።
በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች ሲፈጸሙ እንዳልተፈጸሙ የሚታይበት አገር በመሆኑ፣ ግድያ፣ ውሸት እስር፣ ሰቆቃና አስገድዶ መድፈር በሰፊው የሚፈጸምባት አገር ናት ሲል ዘገባው ጨምሮ ገልጿል።
ከጥቃቱ ሰለባዎች አንዷ የሆነችው፣ “ጀርባዬን፣ ጭኔን፣ ክንዴን ተገርፊያለሁ። ሌሎች እድሚያቸው ከ15-19 ዓመት የሚሆናቸው 5 ሴቶች ከእኔ ጋር ታስረው ነበር። በአሰቃቂ ሁኔታ ሲገረፉና ሲደፈሩ ነበር” ስትል እምባ እየተራጨች ገልጻልች።
የኢትዮጵያ ወታደሮቹ የሴቶቹን አንገት በእጃቸው እንደሚያንቁ፣ በሳንጃ እንደሚወጓቸው፣ የጥቃቱ ሰለባዎች ተናግረዋል። ከሰለባዎቹ አንዷ እንዲህ ትላለች፥ “የኢትዮጵያ ወታደሮች በኤሌክትሪክ አቃጥለውኛል፣ በሳንጃ ወግተውኛል፣ በቃ ሁሉንም የማሰቃያ ስልቶችን ሁሉ ተጠቅመዋል።”
ኢትዮጵያ በመንግስት የሰብዓዊ መብት የተነፈገባት አገር መሆኗ ያወሳው ይኸው ሪፖርት፣ ኢህአዴግ ጉልበት በመጠቀምና በሰዎች ላይ ፍርሃት በመፍጠር በማዕከላዊነት የሚያስተዳድር ገዢ ፓርቲ ነው ሲል ገልጿል።
“የተወሰኑት በረሃት እንዲሞቱ ተደረጉ። ሌሎች በግፍ ተጨፈጨፉ፣ እኛን ያሰሩበት ቦታ በሬሳ የተሞላ ነው።” ስትል ለዘጋቢ ፊልም አቅራቢዎች ተናግራለች።
የጥቃቱ ሰለባዎች፣ የኢትዮጵያ ወታድሮች “ማናችሁንም ቢሆን አንተዋችሁም” በማለት ከብቶቻቸውንና ግመሎቻቸውን እንደወሰዱባቸው፣ ቤቶቻቸውንም እንዳቃጠሉባቸው ተናግረዋል።
እንዴት ዜጎችን ከአደጋ መከላከል ያለበት መንግስት በተቃራኒው ያሳድዳል ያለችው ከአስገድዶ መደፈር ሰለባዎች አንዷ፣ “መንግስት ክብርና ጥበቃ ማድረግ ነበረበት። አሁንም እኛን ማሳደዳቸውን እንዲያቆሙ እንፈልጋለን። አገሬን ሳስብ ሃዘን ይሰማኛል፣ በወህኔ ቤት ያለምንም ጥፋት ታስረው የሚማቅቁ ድሃ ሰዎች ያሳዝኑኛል” ብላለች።
ፊልሙ ግንዛቤ ለመፍጠር እንደተሰራ የተሰራ ነው የተባለው ይህ ዘገባ፣ የእርዳታ ሰጪ አገራት ማለትም አሜሪካ፣ እንግሊዝ፣ እና የአውሮፓ ህብረት ይህን የኢትዮጵያ መንግስት የዘር ማጥፋት ዘመቻው እንዲያቆም ተፅዕኖ እንዲያደርጉ ግፊት ለማድረግ እንደተሰራ ገልጿል።
የአገሪቷን ግማሽ የሚሆነውን የፌዴራል በጀት በተለያዩ ፓኬጆች የሚሰጡት እነዚህ የምዕራብያውያን መንግስታት ይህንን ዘር ማጥፋት ወንጀልን ቸላ ማለታቸው፣ ድርጊቱ እንዲፈጸም እንደፈቀዱ ይቆጠራል ሲል ዘግቧል።