የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን ለመስኖ ልማት ግንባታ ተጨማሪ 90 ሚሊዮን ዶላር አካባቢ መደበ

ኢሳት (ሰኔ 17 ፥ 2008)

ከአመታት በፊት ከ700 ሚሊዮን ብር በላይ ለስኳር ፋብሪካዎች ግንባታ መድቦ ክፍተኛ ኪሳራ ውስጥ የገባው የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን ለመስኖ ልማት ግንባታ ለማካሄድ ተጨማሪ 90 ሚሊዮን ዶላር (ወደ 2 ቢሊዮን ብር) አካባቢ መደበ።

ይህንኑ የመስኖ ግንባታ ለማካሄድ ባራን ግሩፕ የተሰኘ የእስራዔል ኩባንያ ኮንትራት እንደተሰጠው ኩባንያው ይፋ አድርጓል።

61 ኪሎሜትር የሚሸፍነው የግድብ ስራ በ19ሺ ሄክታር መሬት ላይ የሚከናወን ሲሆን ኩባንያው በ 20 ወራቶች ውስጥ አጠናቆ ለማስረከብ ስምምምነት መድረሱን አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን ከስድስት አመት በፊት ከአምስት የሚበልጡ የስኳር ፋብሪካዎችን ለማከናወን ከ700 ሚሊዮን ብር በላይ ቢመድብም አንድም ፋብሪካ ወደስራ መግባት ሳይችል ኮርፖሬሽኑ ለከፍተኛ ኪሳራ መጋለጡ ይታወሳል።

የገንዘቡን መመደብ ተከትሎ መንግስት ሃገሪቱን ባለፈው አመት ስኳር ላኪ ሃገር ለማድረግ እቅድ ይዞ የነበረ ሲሆን፣ በኮርፖሬሽኑ ላይ ያጋጠመውን ኪሳራ ተከትሎ እቅዱ ሙሉ ለሙሉ ሳይሳካ መቅረቱ ታውቋል።

ኪሳራ የደረሰባቸውን እነዚህኑ የስኳር ፋብሪካዎች ወደስራ ለማስገባት የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ተጨማሪ ገንዘብ በመመደብ ላይ እንደሚገኝ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው አካላት አስረድተዋል።

የዚሁ አካል የሆነውና ከአንደኛው የስኳር ፋብሪካ ጎን ለጎን ለሚከናወነው የመስኖ ልማት ግንባታ ወደ 2 ቢሊዮን ብር የሚደርስ ገንዘብ መመደቡን ለመረዳት ተችሏል።

የእስራዔሉ ኩባንያ ግንባታ የሚያካሄድለትን ፋብሪካ በስም ባይጠቅስም ከአዲስ አበባ ምዕራብ አቅጣጫ የሚገኝ መሆኑን ከስምምነቱ በኋላ ባወጣው መግለጫ ይፋ አድርጓል።

የእስራዔሉ ሃፓሌም ባንክ ባራን ግሩፕ ለተሰኘው ኩባንያ ወደ 200 ሚሊዮን ዶላር አካባቢ የሚደርስ ገንዘብ ማቅረቡንም የመስኖ ግንባታውን ለማከናወን ስምምነት የፈጸመው ኩባንያ አክሎ አመልክቷል።

የእስራዔሉ ባንክ ያቀረበው ገንዘብ እስራዔል ሰራሽ ለሆኑ ቁሳቁሶች ማቅረቢያ የሚውል መሆኑን ባራን ግሩፕ አክሎ ገልጿል።

የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን ወደ ስራ ላልገቡ የስኳር ፋብሪካዎች በየወሩ ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ለሰራተኛ ደሞዝ ሲከፍል መቆየቱ ይታወሳል።

ይሁንና በጉዳዩ ዙሪያ በቅርቡ ውሳኔን የሰጠው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ኮርፖሬሽኑ የሰራተኛ ቅጥር እንዳያከናውንና የደረሰውን ኪሳራ በአግባቡ ማጣራት እንዲካሄድበት ወስኗል።