ሰኔ ፲፯ (አሥራ ሰባት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በደቡብ ጎንደር ሊቦ ከምከም ወረዳ ትናንት የመንግስት ተቃዋሚ ሃይሎች ባደረሱት ድንገተኛ ጥቃት 6 ፖሊሶች ሲገደሉ አንድ ብሬን መትረጌስ፣ 4 ክላሽንኮቭ ጠመንጃዎችና በርካታ ቦንቦች ተማርከዋል። ኢሳት ከአምስተርዳም ባስተላለፈው ዜና ጥቃቱን አቶ አረጋ የሚባሉ በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ የመንግስት ተቃዋሚ እንደፈጸሙት ቢዘግብም፣ በአካባቢው ከሚንቀሳቀሱ ሃይሎች ባገኘው አስተማማኝ መረጃ፣ ጥቃቱ የተፈጸመው የተጠቀሰውን ግለሰብ ባካተተው በአካባቢው በተደራጁ የመንግስት ተቃዋሚ ሃይሎች ነው።
ታጣቂዎቹ አስቀድሞ በደረሳቸው መረጃ መሰረት ዝግጅት ሲያደርጉ እንደቆዩና ድንገተኛ ተኩስ ከፍተው ፖሊሶችን እንደገደሉዋቸው ምንጮች ገልጸዋል።
ዛሬ በአዲስ ዘመን ከተማ ከፍተኛ ፍተሻ ሲካሄድ የዋለ ሲሆን፣ በርካታ ነዋሪዎች ታጣቂዎችን አውጡ እየተባሉ ተደብድበዋል፤ የታሰሩ ሰዎች መኖራቸውም ታውቋል ። ከታጣቂዎች በኩል የቆሰለም ሆነ የተማረከ ሰው የለም።
ጥቃቱን የፈጸሙት ታጣቂዎች አርበኞች ግንቦት7 በአገር ውስጥ ያደራጃቸው ሃይሎች መሆናቸውን ለኢሳት የደረሰው መረጃ ያመለክታል።
አርበኞች ግንቦት7 ጥቃቱን በማስመልከት የሰጠው መግለጫ የለም።