የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አባላት ሲገደሉ በክብር አለመቀበራቸው በሶማሊ ክልል ከፍተኛ የስነልቦና ቀውስ እየፈጠረ ነው ተባለ

ሰኔ (አሥራ  ሰባት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የአካባቢው ነዋሪዎች ለኢሳት እንደገለጹት በባይዶዋ፣ ሞቃዲሹና ሌሎችም የሶማሊያ ግዛቶች በአልሸባብ ተዋጊዎች የሚገደሉ የኢትዮጵያ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ፣ በመኪኖች እየተጫኑ በኢትዮጵያና በሶማሊያ ድንበር አካባቢ መጣላቸው በአካባቢው ነዋሪዎች ላይ ከፍተኛ የስነ ልቦና ቀውስ ፈጥሯል።

የበርካታ ወታደሮች አስከሬን እንደ አልባሌ ሜዳ ላይ እየተጣለ በመሆኑ የአውሬ ራት እየሆኑ ነው የሚሉት ነዋሪዎች፣ የወዳደቀ እና በአውሬ የተበላ አስከሬን መመልከት የተመደ ነገር ሆኗል ይላሉ። ማንኛውም ሰው ቢሆን ከሞተ በሁዋላ በክብር ሊቀበር ይገባል፣ በእኛ አካባቢ የምናየው ነገር ግን እጅግ አሳዛኝ ነው የሚሉት ነዋሪዎች፣ ድርጊቱ በአካባቢው ነዋሪዎች ስነልቦና ላይ ትልቅ ተጽኖ እየፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል።

አንዳንድ ነዋሪዎች ችግሩ ትኩረት እንዲያገኝ በሚል የሟች ወታደሮችን ፎቶዎች በፌስ ቡክ  በመልቀቅ ላይ ናቸው።

በሌላ በኩል በደሴ ሰራዊት ለመመልመል የተደረገው ጥረት አለመሳካቱን ተከትሎ የወረዳው አመራሮች ከስልጣን እንደሚነሱ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል።

ውትድርና ምልመላ መስፈርቱ ላይ 8ኛ ክፍል የጨረሰ የሚል መስፈረት የተቀመጠ ቢሆንም፣ የከተማዋ ፖሊሶችና ካድሬዎች ላልተማሩ ወጣቶች “ የትምህርት ማስረጃ እንሰራላችሁዋለን” በማለት እንዲመዘግቡ ለማግባባት ሲደክሙ መሰንበታቸው ታውቓል።

በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ጦርነት ከተነሳ  የኢህአዴግ መንግስት የግዳጅ ወታደራዊ ምልመላ ሊያደርግ እንደሚችል ጉዳዩን በቅርብ የሚከታተሉ ወገኖች ገልጸዋል።