ኢሳት (ሰኔ 16 ፥ 2008)
በደቡብ ሱዳን የሚገኝ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያን በመጠበቅ ላይ የነበሩ የኢትዮጵያ ወታደሮች ስደተኞቹ በታጣቂዎች ሲጠቁ ካምፑን ጥለው መሄዳቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት መርማሪ ቡድን አጋለጠ።
የሩዋንዳ ወታደሮችም ስደተኞቹን ለመታደግ ያልተገባ ጥያቄ ማቅረባቸውም ተመልክቷል። ይሕም ለ40 ሰዎች መገደልና ለ20ሺ ሰዎች መፈናቀል ምክንያት ሆኗል።
አልጀዚራ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ምንጮችን ጠቅሶ እንደዘገበው ድርጊቱ የተፈጽመው በዚህ በፈረንጆቹ አመት መጀመሪያ በየካቲት 2016 ሲሆን የስደተኞቹ ካምፕ የሚገኘውም ማላከል ተብላ በምትጠራው የደቡብ ሱዳን ከተማ ነው።
የደቡብ ሱዳን ሰራዊት ዩኒፎርምን የለበሱ ታጣቂዎች 48 ሺ ስደተኞች ወደተጠለሉበት የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ጣቢያ ለጥቃት ሲመጡ፣ በተባበሩት መንግስታት ደሞዝ የሚከፈላቸውና ስደተኞቹን ከጥቃት የመከላከል ሃላፊነት የተጣለባቸው የኢትዮጵያ ወታደሮች አካባቢውን ጥለው ሄደዋል። እልጀዚራ ያነጋገራቸው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰላም አስከባሪ አዛዦች ድርጊቱ መፈጸሙን አረጋግጠዋል።
የሰላም አስከባሪዎች ተግባር ለአደጋ የተጋለጡ ሰዎችን መጠበቅ እንደሆነ ቢታመንም፣ የሩዋንዳ ወታድሮች ደግሞ ታጣቂዎች ላይ ለመተኮስ የጽሁፍ ትዕዛዝ መጠበቃቸው አነጋጋሪ መሆኑም በሪፖርቱ ተመልክተዋል።
ይህ 40 ስደተኞች የተገደለበትና 20ሺህ የሚሆኑት ደግሞ መኖሪያቸው የተቃጠለበት ድርጊት በተባበሩት መንግስታት መርማሪ ቡድን ቢመረመርም ጉዳዩ ለጸጥታው ም/ቤት እንዳይቀርብ ወይንም ለህዝብ እንዳይገለጽ ጥረቶች መደረጋቸውም በአልጀዚራ ሪፖርት ተመልክቷል።
በጥቃቱ ሁለት አባላቱን ያጣው ዶክተርስ ዊዝ አውት (Médecins Sans Frontières) ቦርደርስ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሃላፊነቱን ባለመወጣቱ ለብዙሃን ህይወት መቀጠፍ ምክንያት ሆኗል በማለት ወቅሰዋል።
የኢትዮጵያ ወታደሮች የተሰጣቸውን ሃላፊነት ትተው፣ ስደተኞቹን ለአደጋ አጋልጠው መሄዳቸውን የተመለከተው ሪፖርት በአሁኑ ወቅት ለተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ም/ቤት መቅረቡንም ከአልጀዚራ ዘገባ መረዳት ተችሏል።