ኢሳት (ሰኔ 16 ፥ 2008)
በቅርቡ ሃላፊነታቸውን በፈቃዳቸው በለቀቁት በአቶ ተገኔ ጌታነህ ምትክ አዲስ የጠቅላይ ፍ/ቤት ፕሬዚደንት ተሾመ። የህወሃት ታጋይ በነበሩ ምክትል ፕሬዚደንት በአቶ መድህን ኪሮስ ምትክ ደግሞ የትግራይ ክልል ጠቅላይ ፍ/ቤት ዳኛ የነበሩ ሃሙስ ሰኔ 16 ፥ 2008 በፓርላማ ተሾመዋል።
አቶ ተገኔ ጌታነህ ተክተው የጠቅላይ ፍ/ቤት ፕሬዚደንት ሆነው የተሾሙት በጠቅላይ ፍ/ቤት በዳኝነት ሲያገለግሉ የቆዩት አቶ ዳኜ መላኩ ሲሆኑ፣ አቶ መድህን ኪሮስን የተኳቸው ደግሞ አቶ ጸጋዬ አስማማው መሆናቸው ተመልክቷል። አቶ ጸጋዬ አስማማው የመቀሌ ዞንና የትግራይ ክልል ጠቅላይ ፍ/ቤት ዳኛ ሆነው ማገልገላቸው የተጠቀሰ ሲሆን፣ የትግራይ ክልል ፕሬዚደንት የህግ አማካሪ ሆነው መስራታቸውም ተመልክቷል።
የህወሃት ታጋይ የነበሩትና በኢህአዴግ የስልጣን ዘመን ረዥም አመታት በዳኝነት ያገለገሉት አቶ መድህን ኪሮስ ከስልጣን የተነሱበት ምክንያት በህወሃት ውስጥ ከተፈጠረው መሳሳብ ጋር በመያያዙ ይሆን አይሁን የታወቀ ነገር ባይኖርም ሪፖርተር ጋዜጣ አቶ መድህን ኪሮስ በጡረታ እንደሚሰናበቱ ዘግቧል።
በኢህአዴግ የስልጣን ዘመን ረጅም ዘመን በጠቅላይ ፍ/ቤት ፕሬዚደንት ያገለገሉት አቶ ከማል በድሪ በጡረታ ሲሰናበቱ እርሳቸውን የተኩት አቶ ተገኔ ጌታነህም 6 አመታት ያህል ካገለገሉ በኋላ በፈቃዳቸው ስልጣናቸውን ለቀዋል።
በቀደሙት ሁለቱ የጠቅላይ ፍ/ቤት ፕሬዚደንት የስልጣን ዘመንም ይሁን አሁን በተሾሙት በአቶ ዳኜ መላኩ ጋር በምክትል ጠቅላይ ፍ/ቤት ፕሬዚደንት የተሾሙት ሶስቱም የትግራይ ተወላጆች መሆናቸው የታወቁ ሲሆን፣ በስልጣን ተዋረድ በምክትልነት ቢቀመጡም ከዚህ ቀደም የነበሩት አቶ መንበረ ጸሃይ ታደሰም ሆነ አቶ መድህን ኪሮስ ይበልጥ ወሳኞች እንደነበሩ ሲገለጽ ቆይቷል።