በኮንሶ አዲስ ውጥረት መንገሱ ተገለጸ

ኢሳት (ሰኔ 15 ፥ 2008)

በደቡብ ክልል ኮንሶ ወረዳ በቅርቡ ከአስተዳደራዊ ጥያቄ ጋር የተነሳው ተቃውሞ ዳግም ቀጥሎ በትንሹ አንድ ነዋሪ መገደሉንና በወረዳዋ አዲስ ውጥረት መንገሱን ነዋሪዎች ለኢሳት ገለጹ።

ለደህንነታቸው ሲሉ ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉት ነዋሪዎች በወረዳዋ ሰፍረው የሚገኙ የጸጥታ ሃይሎች ከአስተዳደራዊ ጥያቄ ጋር ግንኙነት አላቸው የተባሉ ሰዎችን እያሰሩ እንደሆነ ከዜና ክፍላችን ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ አስረድተዋል።

የጸጥታ ሃይሎች በወረዳዋ ዳግም መውሰድ የጀመሩትን እርምጃ ተከትሎ አቶ ጃሚነ አያኖ የተባሉ ነዋሪዎች ተገድለው መገኘታቸውን ነዋሪዎች ከኢሳት ጋር በደረጉት ቃለ-ምልልስ አስታውቀዋል።

በወረዳዋ ያለው የጸጥታ ሁኔታ ለነዋሪዎች ስጋት እየሆነ መምጣቱን የተናገሩት እማኞች ማክሰኞ ከተፈጸመው ግድያ በተጨማሪ በትንሹ ሶስት ነዋሪዎች ለእስር መዳረጋቸውን ገልጸዋል።

የኮንሶ ወረዳ ነዋሪዎች ወረዳዋ የተሻለ እድገት እንዲኖራት በማለት ወደ ዞን እንዲሻገር ሲሉ ጥያቄ ማቅረብ መጀመራቸው ይታወሳል።

ይሁንና የወረዳዋ ነዋሪዎች ያነሱት አስተዳደራዊ ጥያቄ ጉዳዩ ከሚመለከተው አካል ምላሽን ከማግኘት ይልቅ የሃይል እርምጃ እየተሰጠው መሆኑን የወረዳዋ ነዋሪዎች በጉዳዩ ዙሪያ ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ አስረድተዋል።

በወረዳዋ ዳግም የተቀሰቀሰውን ተቃውሞ ተከትሎ የመንግስት አገልግሎት መስጫ ተቋማት ስራቸው ተስተጓጉሎ የሚገኝ ሲሆን ወረዳዋ በወታደራዊ አስተዳደር ውስጥ ትገኛለች ሲሉ ነዋሪዎቹ በወረዳዋ በሚገኙ 42 ቀበሌዎች ያለውን የጸጥታ አስቸጋሪነት ገልጸዋል።

ለእስር ከተዳረጉ ነዋሪዎች በተጨማሪ አራት ሰዎች የገቡበት አለመታወቁንና ግድያ የተፈጸመባቸው ነዋሪ በፌዴራል የጸጥታ ሃይሎች ጥቃት ሰለባ መሆኑን ነዋሪዎቹ አክለው አስረድተዋል።

በወረዳዋ በሚገኙ በርካታ ቀበሌዎች ተቃውሞ መቀዝቀዝን ቢያሳይም የጸጥታ ሃይሎች ዳግም የሃይል እርምጃ መውሰድ መጀመራቸው ተገቢ አለመሆኑን ከኢሳት ጋር ቃለምልልስን ያደረጉ ነዋሪዎች አመልክተዋል።

በወረቀት የጠየቅነው ጥያቄ በመሳሪያ አፈሙዝ ምላሽ ማግኘቱ አግባብ አይደለም ያሉት ነዋሪዎቹ ጉዳዩ የሚመለከተው የመንግስት አካል ሰላማዊ መፍትሄን እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።