ሰኔ ፲፭ (አሥራ አምስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በታስማኒያ ሆባርት ከተማ የገቢ ማሰባሰብ ስራ ለመስራት በሄዱት በትግራይ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ አባይ ወልዱ ጠባቂ ላይ ድብደባ አድርሰሃል በሚል አንድ ወጣት መከሰሱን ሄራልድ ሰን የተባለው የአገሪቱ ጋዜጣ መዘገቡን ተከትሎ ኢሳት ባደረገው ማጣራት ፣ ወጣቱ ላይ ክስ የመሰረተው የሶማሊያ ዜግነት ያለው አብዱ ባራክ አብዲ የተባለ የአቶ አባይ ወልዱ ጠባቂ ሲሆን፣ ፍርድ ቤት በሚቀጥለው ወር መግቢያ ላይ ክሱን እንደሚመለከተው ታውቋል።
የወጣቱ አባት ለኢሳት እንደገለጹት ጠባቂው የተመታው ተቃውሞ ለማድረግ በሄዱበት ወቅት ተቃውሞ ማድረግ አትችሉም በማለቱ ነው። ክሱ ቀላል መሆኑን የገለጹት የወጣቱ አባት፣ ከዚያ ይልቅ ባለስልጣኖቹ የደረሰባቸውን ተቃውሞ ተከትሎ ከተማዋን ለቀው እንዲወጡ በመደረጋቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል።
በታስማኒያ የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ አባላት ለወጣቱ አስፈላጊውን ድጋፍ ለመስጠት መዘጋጀታቸውን ለኢሳት ገልጸዋል። ክሱ በአንድ ግለሰብ ላይ የተቃጣ ሳይሆን፣ በመላው የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ላይ የተቃጣ መሆኑን ፍርድ ቤት ቀርበው እንደሚናገሩ የማህበረሰቡ አመራሮች ገልጸዋል። ጋዜጣው እነ አቶ አባይ ወልዱ በፖሊስ ታጅበው ከከተማው መውጣታቸውን እንዲሁም በኢትዮጵያውያን ዘንድ የተጠሉ መሆናቸውን ዘግቧል።
እነ አቶ አባይ ወልዱ በአውስትራሊያ የገቢ ማሰብሰብ ስራ ለመስራት ቢሄዱም ከኢትዮጵያውያን ባጋጠማቸው ተቃውሞ የተነሳ ዝግጀታቸውን ማከናወን ሳይችሉ ቀርተዋል።